በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
ድሬዳዋ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ)፦ የትምህርትን ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ አበረታች ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ።
በድሬዳዋ አስተዳደር ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ስምንት የቅድመ መደበኛ፣ የሞዴልና የአዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ዛሬ ተጀምሯል።
በአስተዳደሩ በ18 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፉትን ትምህርት ቤቶች ግንባታ ያስጀመሩት የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልዪ ናቸው።
ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በወቅቱ እንዳሉት፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በትምህርት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙት ውጤታማ ተግባራት የትምህርት ፍትሃዊ ተደራሽነትና ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ውጤት እያሳዩ ናቸው።
በተለይም በቅድመ መደበኛ ትምህርት፣ በትምህርት ቤቶች ምገባ እና በሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ላይ የተከናወኑ ተግባራት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት በተግባር ማረጋገጥ ማስቻላቸውን አንስተዋል።
ከለውጡ በፊት በመላው ሀገሪቱ 4ሺህ 100 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንደነበሩ አስታውሰው ከለውጡ በኃላ በገጠርና በከተማ 34 ሺህ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ህፃናት ትምህርትን በጥራት እንዲማሩ መደረጉን ለአብነት አንስተዋል።
ዛሬ በድሬዳዋ የተጀመሩት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በሀገሪቱ 726 ወረዳዎች ተጨማሪ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት በመጪው የትምህርት ዘመን አገልግሎት እንዲጀምሩ ይደረጋል ብለዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገለፃ ስምንት ሚሊዮን ህፃናትን ተጠቃሚ ያደረገው የትምህርት ቤት ምገባ ሀገራዊ መርሃ ግብርም ህፃናት ከትምህርት ገበታ እንዳይለዩና ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ አስችሏል።
ዛሬ በድሬዳዋ በ606 ሚሊዮን ብር ግንባታው የተጀመረውና በአንድ ዓመት የሚጠናቀቀው የሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ጉዞ የሚያጠናክር ይሆናል ብለዋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ የትምህርት ሚኒስቴር በድሬዳዋ ዛሬ መገንባት የጀመራቸው ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነትን ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹን በባለቤትነት በመከታተልና በመደገፍ በተያዘላቸው ጊዜ፣ በጀትና ጥራት እንዲጠናቀቁ አስተዳደሩ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አስታውቀዋል ።
ዘመናዊና ሞዴል ፕሮጀክቶቹ በድሬዳዋ የትምህርት ጥራትን እና ተሳትፎን ለማረጋገጥ የተጀመሩትን ስራዎች በላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚያስችሉ የተናገሩት ደግሞ የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልዪ ናቸው።
በትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተመራው ቡድን ከግንባታ ማስጀመር ጎን ለጎን የድሬዳዋን የትምህርት ቤቶች ምገባ ማብሰያ ማዕከልና ለምገባው መርሃግብር የተዘጋጀውን 18 ሄክታር የፍራፍሬና የአትክልት ማልሚያ ስፍራን ተመልክተዋል።