ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ባህል ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ነው - አቶ መለሰ ዓለሙ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ባህል ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር እየተደረገ መሆኑን በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ገለጹ።

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ 42 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በርካታ ሚሊዮን ዜጎች በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ የተሳተፉበት ታሪካዊ ምርጫ ሆኖ ተጠናቋል።

የአፍሪካ ህብረት፣ የኢጋድ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና በርካታ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም የምርጫውን ሂደት ነጻ፣ ፍትሐዊነትና ገለልተኝነት እማኝነታቸውን በመስጠት አረጋግጠዋል።

በምርጫው ዕለትም ዜጎች ከማለዳው 10 ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት ድርስ በመሰለፍ ጭምር ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት አስመስክረዋል።

በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የፓርቲዎችና የፖሊሲ ብቻ ሳይሆን የሥርዓት ምርጫ ጭምር ነው።

የዴሞክራሲ ተቋማትና ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃና ገለልተኛነታቸውን በተግባር ያረጋገጡበት ምርጫ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን እውነተኛ ዴሞክራሲ መሻታቸውን ለወዳጅም ለጠላትም ያሳዩበት መሆኑን ገልጸው፤ ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ የተዋንያን ቅንጅት መንጸባረቁንም አድንቀዋል።

ምርጫው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድር ባለፈ ብሔራዊ ክብርና ሉዓላዊነት የተንጸባረቀበት በመሆኑ ኢትዮጵያ አሸንፋለች ብለዋል።

ከለውጡ ማግስት የተደረገው መጠነ ሰፊ የፖለቲካ ሪፎርም የፓርቲዎችን እንግልትና ስደት በማስቀረት ጤናማ የፖለቲካ የፉክክር ምኅዳር መፈጠሩን ገልጸዋል።

የሕግና ፖሊሲ ማሻሻያም በስድስተኛውና በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የፓርቲዎችን ተሳትፎ በማሳደግ አዲስ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እንዲወለድ ማድረጉን አስረድተዋል።

ይህም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥልጣን ምንጭ ከህዝብ የሚሰጥ ድምፅ መሆኑን በመገንዘብ በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ገንቢ ሚና የሚወጡበትን ዕድል መፍጠሩን አብራርተዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም የፖለቲካ ፓርቲዎች የውስጥና የውጭ ጫናን በመቋቋም ጭምር ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ አሻራቸውን ላሳረፉ አካላት ምሥጋና አቅርበዋል።

የለውጡ መንግሥት በሀገራዊ የጋራ ጥቅሞች ላይ ከፉክክር ይልቅ በትብብር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ሥርዓት በመዘርጋት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በብሔራዊ ጥቅም ላይ ወጥ የሆነ አቋም እንዲይዙ አድርጓቸዋል ብለዋል።

ይሄ ትልቅ የዴሞክራሲ ትሩፋት መሆኑን በማንሳት፤ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው በፓርቲዎች መካከል መተማመን በመፍጠር የኢትዮጵያን መዳከም የሚሹ ኃይሎችና ታሪካዊ ጠላቶችን ማሳፈሩን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም