ሀገራት ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የሚያጋብሱበት የዓለም ዋንጫ ክብረ ወሰን ሽልማት - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራት ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የሚያጋብሱበት የዓለም ዋንጫ ክብረ ወሰን ሽልማት
በሙሴ መለሰ
23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ጣምራ አዘጋጅነት መካሄድ ጀምሯል።
የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ በበርካታ ነገሮች «የመጀመሪያ» የተሰኙ አዳዲስ ነገሮችን ይዟል።
ከነዚህም መካከል ለውድድሩ ተሳታፊ ሀገራት የሚበረከተው የገንዘብ ሽልማት ነው።
የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ለዓለም ዋንጫው ተሳታፊ ሀገራት 871 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ሽልማት ማዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል።
ይህም በውድድሩ የ96 ዓመታት ታሪክ ከፍተኛ የሚባለው ነው።
የፊፋ ምክር ቤቱ እ.አ.አ ዲሴምበር 2025 በኳታር ዶሃ ባካሄደው ስብሰባ፤ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ላይ ለሚሳተፉ አገራት የሚከፋፈል የ727 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ታሪካዊ በጀት አጽድቆ ነበር።
ይህ መጀመሪያ ላይ የጸደቀው የገንዘብ መጠን፣ በኳታር አስተናጋጅነት ከተካሄደው የ2022 የዓለም ዋንጫ ጋር ሲነጻጸር የ50 በመቶ ብልጫ ያለው እንደነበር ተገልጿል።
በዚሁ የኳታር ስብሰባ ላይ በጸደቀው ስሌት መሠረት፣ የውድድሩ ሻምፒዮን (ባለድል) 50 ሚሊዮን ዶላር ሲያገኝ፣ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ የሚያጠናቅቀው ቡድን 33 ሚሊዮን ዶላር፣ ሦስተኛው 29 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም አራተኛ ደረጃን የሚያገኘው 27 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦለታል።
በተመሳሳይ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ደረጃ የሚይዙት 19 ሚሊዮን ዶላር፣ ከ9ኛ እስከ 16ኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጡት 15 ሚሊዮን ዶላር፣ ከ17ኛ እስከ 32ኛ ደረጃ ያላቸው ቡድኖች 11 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከ33ኛ እስከ 48ኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁት አገራት እያንዳንዳቸው 9 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ ያገኛሉ።
በተጨማሪም በእያንዳንዱ ደረጃ ላይ ለሚገኙት ቡድኖች ከሚሰጠው የሽልማት ገንዘብ ውጪ፣ ለእያንዳንዱ ተሳታፊ አገር ለዝግጅት ወጪ (Preparation costs) 1.5 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ የነበረ ሲሆን፤ በዚህም ማንኛውም ተሳታፊ አገር ቢያንስ 10.5 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱ ተረጋግጦ ነበር።
ነገር ግን ምክር ቤቱ ውድድሩ ከመጀመሩ 44 ቀናት በፊት፣ እ.አ.አ ኤፕሪልክ 2026 በቫንኩቨር ካናዳ ባደረገው ሌላኛው ስብሰባው ተጨማሪ ማሻሻያ አድርጓል።
ውድድሩ ባስመዘገበው ከፍተኛ የንግድ ገቢ ምክንያት፣ ምክር ቤቱ ቀደም ሲል አጽድቆት በነበረው በጀት ላይ ተጨማሪ የ15 በመቶ ጭማሪ በማድረግ አጠቃላይ ድምሩን ወደ 871 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ አድርጎታል።
በዚህ የቫንኩቨር ስብሰባ በተወሰነው አዲስ ማሻሻያ መሠረት፦
- ለእያንዳንዱ አገር የሚሰጠው የዝግጅት ወጪ (Preparation money) ከ1.5 ሚሊዮን ዶላር ወደ 2.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲያድግ ተደርጓል።
- ለውድድር ተሳትፎ (Qualification money) ከ9 ሚሊዮን ዶላር ወደ 10 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል።
ይህም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 አገራት በሚሳተፉበት በዚህ የዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፍ ማንኛውም አገር፣ ከምድብ ማጣሪያው ባያልፍ እንኳ በትንሹ 12.5 ሚሊዮን ዶላር (የ2.5 ሚሊዮን ዝግጅት እና የ10 ሚሊዮን የተሳትፎ ክፍያ) ያገኛል።
በተጨማሪም ለቡድኖች ልዑካን ቡድን ወጪ መሸፈኛ እና ለትኬት ድልድል ከ16 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ ድጎማ መመደቡ ተገልጿል።
የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ ፊፋ በአሁኑ ወቅት በታሪኩ እጅግ ጠንካራ በሆነ የፋይናንስ አቋም ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ይህም ሁሉንም አባል ማኅበራት ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ለመደገፍ እንዳስቻለ ገልጸዋል።
ይህ ውሳኔም የፊፋ ሀብት እንዴት በቀጥታ ወደ እግር ኳሱና ለዘርፉ ዕድገት መልሶ ጥቅም ላይ እንደሚውል የሚያሳይ ትልቅ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
ከተሳታፊ ቡድኖች ክፍያ የተረፈው አጠቃላይ ገቢ፣ በ211 የፊፋ አባል ማኅበራት አማካኝነት ለዓለም እግር ኳስ ዕድገት ማስፈጸሚያ በድጋሚ ጥቅም ላይ እንደሚውል ፊፋ አስታውቋል።