በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉትን ችግኞች የመንከባከብ ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉትን ችግኞች የመንከባከብ ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል
ግምቢ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ):-በምዕራብ ወለጋ ዞን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉትን ችግኞች ለመንከባከብ ስራ ትኩረት መሰጠቱን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።
የምዕራብ ወለጋ ዞን አመራሮች እና የዞኑ ነዋሪዎች የተሳተፉበት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በመንዲ ከተማ ዛሬ ተጀምሯል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፈ እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄን ስኬታማ ለማድረግ የተተከሉ ችግኞችን በአግባቡ መንከባከብ ከሁሉም ይጠበቃል።
ለመርሃ ግብሩ ስኬታማነትም እንደ ዞን በቂ የችግኝ ዝግጅት፣ ተገቢው የቦታ መረጣ እና የችግኝ መትከያ ጉድጓድ መቆፈሩን ገልጸዋል።
በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከተዘጋጁት 328 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ ለምግብነት እና ለገቢ ምንጭ የሚያገለግሉ የፍራፍሬ፣ የቡና እና የእንስሳት መኖ ችግኞች ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑን አቶ ተሊላ አስገንዝበዋል።
ባለፉት ዓመታት በመርሃ ግብሩ የተተከሉ ችግኞች አብዛኛዎቹ ጸድቀው ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ማስገኘታቸውንም ዋና አስተዳዳሪው አረጋግጠዋል።
ከመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል አባገዳ አምቢሳ ሊካሳ በሰጡት አስተያየት፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኞችን እንደ ሰው ልጅ ተንከባክቦ ማሳደግ የትውልዱ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በየዓመቱ አሻራቸውን በማኖራቸው ልዩ ደስታ እንደሚሰጣቸው ገልጸው፣ ችግኞችን ከመትከል ባሻገር የጽድቀት ሂደታቸውን በአግባቡ እንደሚከታተሉም ተናግረዋል።
አቶ ኤሊያስ ቱቾ በበኩላቸው፤ ችግኝ መትከል በርካታ ጠቀሜታ እንዳለው በመገንዘብ በችግኝ ተከላው እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
በየዓመቱ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የተናገረው ደግሞ ወጣት ኩርፈሳ ኦልጂራ ነው።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ከ200 በላይ የፍራፍሬ ችግኞችን በግሉ ለመትከል ማቀዱንም ጠቁሟል።