ቀጥታ፡

ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት በተሟላ ስነ-ምግባርና ስብዕና ተግባር ላይ ማዋል ይጠበቅባቸዋል

ነቀምቴ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ)፦ ተመራቂዎች የቀሰሙትን እውቀት በተሟላ ስነ-ምግባርና ስብዕና ተግባር ላይ ሊያውሉት ይገባል ሲሉ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ለማ (ዶ/ር) አመለከቱ።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 920 ተማሪዎች አስመርቋል።


 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ለማ (ዶ/ር) በምረቃው ወቅት እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው የተሳካ የመማር ማስተማር ስራ እያከናወነ ይገኛል።

የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ የሥራ ገበያው የሚፈልገውን ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው የተቀበላቸውን ተማሪዎች እውቀትና ክህሎት አስታጥቆ እያስመረቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተመራቂዎችም የቀሰሙትን እውቀት በተሟላ ስነ-ምግባርና ስብዕና ሊተገብሩት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዩኒቨርሲቲው በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የአካዳሚክ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት መልካ ሂካ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በነቀምቴ፣ ጊምቢ እና ሻምቡ ካምፓሶች ትምህርታቸውን የተከታተሉ 920 ተማሪዎችን ማስመረቁን ገልጸዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከልም የመጀመሪያ ዲግሪ 674፣ ሁለተኛ ዲግሪ 218፣ ሶስተኛ ዲግሪ 8 እና በሕክምና ስፔሻሊቲ 20 ተማሪዎችን ማስመረቁን ተናግረዋል።

ተመራቂዎች በተለይም የሥራ ጠባቂነትን አስወግደው ሥራ ፈጣሪ በመሆን ከራሳቸው አልፈው ለሕዝብና ለሀገር ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው በቀሰሙት እውቀት ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ከዩኒቨርሲቲው በፋርማሲ ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 98 በማስመዝገብ የማዕረግ ተመራቂ የሆነው ዱሬሳ ደንቦባ፤ በተማረበት የሙያ መስክ ሀገሩን ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግሯል።

በተለይም ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችሉ በጥናትና ምርምር የታገዙ አዳዲስ ሥራዎችን ለመስራት መዘጋጀቱንም ገልጿል።

የሕግ ትምህርት ክፍል ተመራቂ ገለታ ጋዲሳ በበኩሉ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ያገኘውን እውቀት በመጠቀም በፍትህ ዘርፉ ላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ መዘጋጀቱን ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም