በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ117 ሺህ በላይ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል- መምሪያው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ117 ሺህ በላይ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል- መምሪያው
ደብረ ማርቆስ ፤ሰኔ 18/2018(ኢዜአ)፡- በምስራቅ ጎጃም ዞን ባለፉት 11 ወራት ከ117 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ስራና ክህሎት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ፀሐይ ቦጋለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር የተቻለው የአካባቢውን ጸጋ በጥናት በመለየትና አልምቶ ለመጠቀም በተደረገ ጥረት ነው።
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከ 131 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን ባለፉት 11 ወራት 117 ሺህ 427 የሚሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
የተፈጠረው የስራ እድል በማዕድን ልማት ፣ በኮንስትራክሽን ፣ በግብርና ፣ በአምራች ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች መስኮች መሆኑን ነው የጠቆሙት ።
በዚሁ ወቅት የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት በተለያዩ መስኮች ትምህርታቸውን ተከታትለው የተመረቁ መሆናቸውንም አንስተዋል።
የስራ እድል ለተፈጠረላቸው ዜጎች 491 ሚሊየን ብር በላይ ብድር፣ ከ270 በላይ የመስሪያ ሼድና ኮንቴነሮች ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በገጠርና በከተማ በግብርና ዘርፎች ስራ ለተፈጠረላቸው ዜጎች ከ15 ሺህ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት በመስጠት ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን አብራርተዋል።
በዞኑ የባሶሊበን ወረዳ የጁቤ ከተማ ነዋሪ ወጣት ቀለምወርቅ ገነት ፤ ከሶስት ጓደኞቹ በመደራጀት ወደ ግብርና ስራ ገብቶ ተጠቃሚ መሆን መጀመሩን ነው የሚናገረው ።
የተፈጠረለት የስራ እድል ከቤተሰብ ጥገኝነት በማውጣት ገቢ ለማግኝት ከማስቻሉ ባሻገር ሀብት ለማፍራት እንዳስቻለው ነው ያመለከተው።
የአዋበል ወረዳ የሉማሜ ከተማ ነዋሪ ወጣት ጌትነት ይመር በበኩሉ፤በዘንድሮው ዓመት ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመደራጀት በኮንስትራክሽን ዘርፍ የብሉኬት ምርት ላይ መሰማራቱን ነው የሚናገረው።
በመንግስት በተመቻቸላቸው የመስሪያ ቦታን ጨምሮ የ500 ሺህ ብር ብድርና ሌሎች ድጋፎች በመነሳት ወደ ስራ ተሰማርተው ገቢ ማግኝት መጀመራቸውን ነው የሚናገረው።