ችግኞችን አዘጋጅተን በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችን አድጓል-ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ችግኞችን አዘጋጅተን በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችን አድጓል-ወጣቶች
ሀዋሳ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል ለአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርና ለኮሪደር ልማት የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች አዘጋጅተው በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆኑን በችግኝ ብዜት ሥራ የተሰማሩ ወጣቶች ተናገሩ።
በክልሉ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች አዘጋጅተው በማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ባለፈ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙም በማድረግ በኩልም አስተዋጾ እያደረጉ ነው።
በተለይ ለአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ስኬታማነት ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ችግኞችን እያቀረቡና የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እየሆኑም መጥተዋል።
በማህበር ተደራጅተው የፍራፍሬ፣ የውበትና የጥላ ዛፍ ችግኞችን አዘጋጅተው በማቅረብ ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች መካከል የድሪመርስ ላንድ ስኬፒንግና ሲድሊንግ ማህበር አባላት ይገኙበታል።
የማህበሩ ሥራ እስኪያጅ ኮከብ ቢያድግልኝ (ዶ/ር) አምስት ሆነው በ50 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የችግኝ ማፍላትና ማቅረብ ሥራቸውን ጀምረው በአሁኑ ወቅት ካፒታላቸውን 500 ሺህ ብር ማድረስ ችለዋል።
በስራቸው የማህበሩ አባላት ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን የገለጸችው ኮከብ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅትም ለሌሎች አምስት ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉም ተናግራለች።
በማህበሩ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ወጣት ባዩ በየነ እንዳለው፣ በማህበሩ በተፈጠረለት የሥራ ዕድል ገቢ እያገኘ ራሱን ማስተዳደር ችሏል።
የሲዳማ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አበባየሁ በየነ እንዳሉት፣ በክልሉ በየዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተለያዩ ችግኞችን በመትከል የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙና የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በዘንድሮው የክረምት አረንጓዴ አሻራ መረሀ ግብር የፍራፍሬ፣ የቡና፣ የቀርከሃና ሌሎች አገር በቀል ዝርያ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጎ ወደተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
በክልሉ በክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን ለማሳተፍ መታቀዱን ጠቅሰዋል።
ለተከላ ከተዘጋጁት ችግኞች ውስጥ አቮካዶ፣ አፕል፣ ማንጎ፣ ቡናና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች እንዲሁም ቀርከሀ፣ ቀረሮ፣ ዋንዛና መሰል ሀገር በቀል ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል።
ችግኞቹ በ316 የመንግስት፣ የማህበራትና አርሶ አደሮች የችግኝ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን የተናገሩት አቶ አበባየሁ፣ ይህም አርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ ከማድረግ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ የሚተከሉት የፍራፍሬ ችግኞች በቀጣይ ለምርት ሲደርሱ ለኢንዱስትሪ ፓርክ ግብዓት እንዲሆኑ ታስቦ የተዘጋጁ መሆኑንም ገልጸዋል።