የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻሻሉ ረቂቅ አዋጆች መርምሮ በሙሉ ድምፅ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻሻሉ ረቂቅ አዋጆች መርምሮ በሙሉ ድምፅ አጸደቀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ):- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመረጃ ነፃነት አዋጅ እና የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የማሻሻያ ረቂቅ አዋጆችን አጽድቋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 28ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የ2018 በጀት ዓመት የ11 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፓርት አዳምጧል።
እንዲሁም የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመረጃ ነፃነት አዋጅን አስመልክቶ ያቀረበውን የሪፓርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አፅድቋል።
የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ በወቅቱ፤ ረቂቅ አዋጁ የዜጎችን መረጃ የመጠየቅና ማግኘት መብት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
አዋጁ አለም አቀፍ መብቶችን በመጠበቅ ፈጣን ቀልጣፋና ወቅቱ የጠበቀ መረጃ ፍሰት የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም የሀገራችንን ብሄራዊ ደህንነት በሚያረጋግጥ መልኩ የተዘጋጀ በመሆኑ ምክር ቤቱ እንዲያጸድቀው ጠይቀዋል።
ይህን ተከትሎም አዋጅ ቁጥር 1427/2018 ሆኖ ተሻሽሎ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አዋጁን አፅድቋል።
የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያን የፍትህ ሥርዓት በማሻሻል ረገድ እጅግ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል።
የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ለማቋቋም፣ የፍርድ ቤቶችን የሥራ ተደራሽነት ይበልጥ ለማስፋት እንደሚረዳም ጠቁመዋል።
በዚህም አዋጅ ቁጥር 18/2018 ሆኖ ተሻሽሎ በሙሉ ድምፅ ጸድቋል።