ቀጥታ፡

በምርጫው ካሸነፈው ብልፅግና ፓርቲ ጋር በብሔራዊ ጥቅም እና በትልልቅ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ ነን -የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ):- በምርጫው ካሸነፈው ብልፅግና ፓርቲ ጋር በብሔራዊ ጥቅም እና በትልልቅ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው 7ኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የተሳተፈበትና በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፉክክር መድረክ የሆነበት ታሪካዊ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።

በምርጫው ሂደት ላይ የህዝቡም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ብስለትና አስተዋይነት በግልጽ የታየበት በመሆኑ፣ ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሊጠናቀቅ ችሏል።

የምርጫውን ውጤት ተከትሎም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለአሸናፊው ብልፅግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት እያስተላለፉ የሚገኙ ሲሆን፣ በቀጣይም ለሀገር ልማትና አንድነት በጋራ ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት በመግለጽ ላይ ናቸው።

የኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እንዳስታወቁት፤ የምርጫ ሂደቱ ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት መሆኑን ህዝቡ ለምርጫው ውጤታማነት ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ ያሳየው ተሳትፎ እጅግ አስደናቂ ነበር፡፡

በምርጫ ወቅትም በነቂስ በመውጣት በሰለጠነ አግባብ በሰላማዊ ሁኔታ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመንግስት ስልጣን መያዝ የሚገባ መሆኑን ትልቅ ትምህርት መስጠት መቻላቸውን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሴቶች መምሪያ ሃላፊና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሴቶች ክንፍ ስራ አስፈጻሚ እመቤት ቢራራ እንዳሉት፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች በነቂስ ወጥተው የመረጡበት ታሪካዊ ሂደት ነው።

ሴቶችም ከማለዳው ጀምሮ በከፍተኛ ተነሳሽነት በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት መሳተፋቸውን ጠቁመው፤ ሴቶች በከፍተኛ ቁጥር በምርጫው መሳተፋቸውን አንስተዋል፡፡

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ነጻነት ጣሰው በበኩላቸው፤ በጠቅላላ ምርጫው የታየው ሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ ለዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከርና ለሀገረ መንግስት ግንባታ ፅኑ መሰረት የጣለ መሆኑን አስታውቀዋል።

መንግስት አካታችነት ላይ በትኩረት በመስራቱ በርካታ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ሴቶች፣ ወጣቶች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሂደቱ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ የተደረገው ጥረት ለምርጫው ስኬታማነትና ተአማኒነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል።

በቀጣይ ፓርቲው ህዝባዊ አደራን ተቀብሎ መንግስት ለመሆን ከበቃው ብልፅግና ፓርቲ ጋር በልማት እና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሴቶች መምሪያ ሃላፊና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሴቶች ክንፍ ስራ አስፈጻሚ እመቤት ቢራራ ኢዜማ በብሔራዊ ጥቅም በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከአሸናፊው ብልፅግና ፓርቲ ጋር በቅርበትና በትብብር ለመስራት ሙሉ ቁርጠኝነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የሁላችንም ተወዳዳሪዎች የጋራ መኖሪያ በመሆኗ ለላቀ እድገቷ በጋራ መስራት ይገባናል ያሉት ደግሞ የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ነጻነት ጣሰው ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም