በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች 117 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች 117 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ):- በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች 117 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስራት ጤራ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ኢትዮጵያ የተለያዩ የእንስሳት ምርትና ተዋጽኦን በማቀነባበር ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ታገኛለች፡፡
የኢትዮጵያ የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስራት ጤራ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የእንስሳት ሀብት ተገቢውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንድታገኝ የእንስሳትን ምርታማነት የሚያሳድጉ አሰራሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡
ኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ዝርያዎችን ለማሻሻል አዳዲስ የፈሳሽ ናይትሮጅን ማምረቻ ማዕከላትን እያሰፋና ነባሮችን እያዘመነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ለውጭ ገበያ ካቀረባቸው የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች 117 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፤ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የስድስት ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አለው ብለዋል፡፡
ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች መካከል የበግና ፍየል ስጋ እንዲሁም የእርድ ተረፈ ምርቶች ቀዳሚዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የሥጋ ምርቶቹ በብዛት ወደ ውጭ ከተላኩባቸው ሀገራት መካከል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታር መሆናቸውን ገልጸው፤ ወደ አፍሪካ ሀገራትም ይቀርባሉ ብለዋል፡፡
በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል የእንስሳት ጤና እና ሥነ ተዋልዶ ተመራማሪ ዶክተር ቸኮል ደምስ፤ የእንስሳት ምርታማነትን ለማሳደግ በዘርፉ ለተሰማሩ ዜጎች የእንስሳት እርባታ ሳይንስ ላይ በቂ ግንዛቤ እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡
ማዕከሉ የተሻሻሉ የበግና የዳልጋ ከብት ኮርማዎች ተገቢውን እንክብካቤ አግኝተው እንዲያድጉ ለማድረግ በምርምር የተደገፈ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል የእንስሳት ጤና ማሻሻያ ተመራማሪ ዶክተር ናሆም በላይ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የእንስሳት ሀብት ልማትን የሚያሳድግ ፍሬያማ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የዘርፉ ባለሙያዎች ልምዳቸውን ለእንስሳት ሀብት ልማት ማዋል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡