ቀጥታ፡

የወጣቶችን ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት በበጎ ሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ማፍራት የሚያስችል ምኅዳር ፈጥረዋል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት በበጎ ሥነ-ምግባር የታነጸ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራት የሚያስችል ምኅዳር መፍጠራቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሀገራዊ ለውጡ ማግስት በመልካም ስብዕና የተቀረጸ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ይገኛል።

ሀገር አቀፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶችም ከተሞችን ከማስዋብ ባሻገር ወጣቶችና ሕፃናት በአካልና በአዕምሮ የሚቀረጹበትን ምቹ የሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት እንዲገነቡ ዕድልን ፈጥረዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አሕመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት ለወጣቶችና ሕፃናት ስብዕና ግንባታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

ለዚህም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወጣቶች ፖሊሲ በማሻሻል፣ የወጣቶችና ሕፃናትን ስብዕና ግንባታ ማሳደግ በሚያስችል መልኩ እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።


 

የወጣቶች ስብዕና ልማት ስትራቴጂን በመቅረጽ ጭምር ለሀገር ግንባታ መሰረት የሚሆን ትውልድ ለማፍራት በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ከተሞች የኮሪደር ልማት የፈጠረው የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ግንባታም ለበርካታ ወጣቶችና ሕፃናት አስቻይ ምህዳር መፍጠሩን አስረድተዋል።

በተለይም ለሕፃናትና ታዳጊዎች የተፈጠሩት የመጫወቻና መዝናኛ ማዕከላት የመሰረተ ልማት አስቻይ ምኅዳር፣ በበጎ ሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ጉልህ ፋይዳ እያበረከቱ መሆኑን አስረድተዋል።

በበጎ ስብዕና የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ከቤተሰብ እስከ ባለድርሻ ተቋማት ጋር የሚከናወኑ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን አቅም፣ ጥራትና ተደራሽነት የማስፋፋትና የማሻሻል ሥራም ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።

የስብዕና መገንቢያ ማዕከላትንም ወደ ማህበራዊ ኢንተርፕራይዝ በማሳደግ የገቢ አቅማቸውን ለማሻሻል እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም