ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም ያልደከሙ ልቦች

ምድረ ቀደምቷ ሀገር ኢትዮጵያ በሀገርነት ቀድማ ብትገኝም ከስልጣኔ ፈር ወደ ኋላ መቅረቷ ይወሳል።

ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮች ደግሞ በስልጣኔ ጎዳና ወደፊት እንዳትራመድ እግር ከወርች አስረዋት የቆዩ ጉዳዮች መሆናቸውም ይታወቃል ።

ለዘመን ዘለል የቅራኔና አለመግባባት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን በሰለጠነ ሀገራዊ የምክክር ሂደት በዘላቂነት ዕልባት ሰጥቶ ኢትዮጵያ የነገ መሻቷን ዕውን ታደርግ ዘንድ ታዲያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደስራ ከገባ ጥቂት ዓመታት አልፈዋል።

ሂደቱንና ኮሚሽኑን ለመምራት ደግሞ ዕድሜ እና ዕውቀት ጠገብ ኮሚሽነሮች ተሹመው ያለመታከት ሲሰሩ ቆይተዋል።

ኮሚሽነሮችም ባለፉት ዓመታት በነበሩ የምክክር ሂደት የተጠቃለሉ ስምንት አጀንዳዎችን ትናንት ማምሻውን ይፋ አድርገዋል።

ኢትዮጵያን በጽኑ መሰረት ላይ የማቆም ሂደትን እንዲመሩ የተሰጣቸውን ክብርና ከባድ ሀላፊነት የተረዱት እነዚህ ኮሚሽነሮች ያለምንም ድካም መድረክ ላይ ተሰድረው ቆመው አጀንዳዎቹን ይፋ ያደረጉበት አጋጣሚ ደግሞ በበርካቶች ዘንድ ከበሬታ አስችሯቸዋል።

አብዛኛዎቹ ኮሚሽነሮች ሀገራቸውን በተለያዩ ሃላፊነቶች ዕድሜ ዘመናቸውን ያገለገሉት አንጋፋ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።

የእነዚህ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ድርጊት ዛሬም በማመሻ ዕድሜያቸው ሀገራቸውን ለማገልገል ያላቸውን ውስጣዊ ጽኑ መሻት ያረጋገጠና ለኢትዮጰያ ሕልውና የሚበጅ ብሔራዊ መግባባት የመፍጠር ትጋትና ቁርጥኝነትን የገለጠ አጋጣሚ ነው።

ሀገር በጽኑ መሰረት ላይ የምትቆመው ሁሉም ዜጋ ዕውቀት፣ ጥበብና ሃላፊነት ሲያዋጣ እንደሆነ ኮሚሽነሮቹ ሁነኛ ማሳያ ናቸው።

የኢትዮጵያ የዘመን ዕንቆቅልሽ የሚፈታው፣ የሀገረ መንግስት ግንባታዋ የሚሳለጠው፣ በስልጣኔ ጎዳናዋ ላይ የተጋረጡ ጉድፎችና እንከኖች የሚነጹት በስልጡን ሀገራዊ ውይይትና ምክክር ብቻ መሆኑን ልባቸው የነገራቸው፣ ዕውቀትና ዕድሜ ያስተማራቸው አርዓያዎችም ናቸው፡፡

Ethiopian News Agency #ምክክር #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም