ርዕስ መስተዳድር አረጋ ከበደ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን በሰሜን ጎጃም ዞን በመገኘት አስጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ርዕስ መስተዳድር አረጋ ከበደ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን በሰሜን ጎጃም ዞን በመገኘት አስጀመሩ
ባህርዳር፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ)፡- የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳድር አረጋ ከበደ የዘንድሮውን የክረምት አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ እንጉቲ ቀበሌ በመገኘት አስጀምረዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ባስጀመሩት የዘንድሮው ክረምት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል መሐመድ ተሰማ ተገኝተዋል።
በክልሉ በክረምቱ ወቅት ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል።
በክልሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተካሄደ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የደን ሃብት ሽፋኑን ከማሻሻል ባለፈ የአፈር መከላትን ማስቀረት እንዲሁም የተፈጥሮ ሚዛንን መከላከል መቻሉም ተመላክቷል።
አርሶ አደሩም ተፋሰሶች በመልማታቸው በመስኖ፣ በእንስሳት ማድለብና ማርባት፣ በንብ ማነብ፣ በመኖ ልማትና በሌሎች የግብርና ዘርፎች ምርታማነቱን ለማሳደግ ችሏል።
የተገኘውን ጥቅም አጠናክሮ ለማስቀጠልም በዘንድሮው ክረምት ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ የደን፣ የፍራፍሬና የውበት ችግኞችን በማዘጋጀት መርሃ ግብሩን አስጀምረዋል።
የተዘጋጀውን ችግኝም ህብረተሰቡን በማሳተፍ በ261 ሺህ 460 ሄክታር መሬት ላይ በመትከል የመንከባከብ ስራ ይሰራልም ተብሏል።
በችግን ተከላ ፕሮግራሙ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የመከላከያና ሌሎች የክልል አመራሮች ተሳትፈዋል።