የጅማ ከተማ ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሥራ ዕድል አግኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የጅማ ከተማ ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሥራ ዕድል አግኝተዋል
ጅማ፤ ሰኔ 18/2018(ኢዜአ)፡- በየዓመቱ እየተከናወነ በሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የጅማ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች ወጣት ሒካ መኮንን፤ ከዚህ ቀደም ያለምንም ሥራ በቤተሰቦቹ ላይ ጥገኛ እንደነበር ተናግሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሕይወቱ ትልቅ ተስፋ እንደሆነለት ይገልጻል።
ወጣት ሒካና ጓደኞቹ በማኅበር ተደራጅተው ችግኝ በማፍላት ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በማዘጋጀት በየዓመቱ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ተናግሯል።
በተለይም ከዚህ ቀደም ለከተማ ውበት ተብለው ከሌሎች አካባቢዎች ይመጡ የነበሩ ችግኞችን እያፈሉ በስፋት እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው ወጣት አብዱልከሪም ያሲን በበኩሉ በችግኝ ማፍላት ሥራ በሚያገኘው ገቢ ራሱን እያስተዳደረበት መሆኑን ተናግሯል።
በትጋት ሠርተን የተለያዩ የፍራፍሬና ለከተማ ውበት የሚሆኑ ችግኞችን ማዘጋጀታችን ተመራጭ እንድንሆን አድርጎናል፤ ወደፊትም ይህንን በማጠናከር ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን እንሠራለን ብለዋል።
ሌላኛው ወጣት እስማኤል ቦሪ ደግሞ በአረንጓዴ አሻራ በተፈጠረለት የሥራ ዕድል ከራሱ አልፎ ቤተሰቦቹን ማገዝ መቻሉን ገልጾ፤ አረንጓዴ አሻራ ንጹሕ አየር ከመስጠት ባለፈ፣ የሥራ ዕድልና የሀገርን ኢኮኖሚ የሚደግፍ ትልቅ አቅም ነው ብሏል።
የጅማ ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቶፊቅ ጊዲ፣ ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ የሥራ ዕድል ከማግኘት ባለፈ፣ ለከተማዋ ውበትና ገጽታ ግንባታ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በ12 ማኅበራት የተደራጁ ወጣቶች የዚህ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ለሥራቸው የሚረዱ አስፈላጊ ድጋፎችን የማድረግ ሥራም እየተከናወነ እንደሚገኝ አክለዋል።
በጅማ ከተማ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱ ታውቋል።