ቀጥታ፡

የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ እምርታ እየታየ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ):- የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በመደገፍ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ትልቅ እምርታ እየታየ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የዲጂታል አግሪካልቸር ሰርቪስ ፕሮጀክት ዲንና ተመራማሪ አቶ ተመስገን ገበየሁ ገለጹ፡፡

የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርና ዘርፍ በቴክኖሎጂ በመደገፍ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የዲጂታል አግሪካልቸር ሰርቪስ ፕሮጀክት ዲንና ተመራማሪ አቶ ተመስገን ገበየሁ፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ አማካኝነት ግብርናን ለማዘመን ቴክኖሎጂ በስፋት ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል።

በዚህም አርሶ አደሮች በእጅ ስልካቸው በመጠቀም ስለ ግብዓቶች አቅርቦት፣ ዋጋ እና ጊዜ መረጃ እንዲሁም ስለ አፈር፣ ዝናብና የሰብል በሽታዎች የባለሙያ ምክር በቀላሉ እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ይህ የዲጂታል ስልት አርሶ አደሩ የገበያ ዋጋን አስቀድሞ አውቆ ምርቱን በቀጥታ እንዲያቀርብ በማገዝ ምርታማነቱንና ተጠቃሚነቱን በተግባር እንዲያረጋግጥ ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ቅርጽ ለማስያዝና ፕሮግራሞችን ለመደገፍ በከፍተኛ ሁኔታ ሲጠቀምበት መቆየቱን ተመራማሪው ጠቁመዋል።

በተለይም የምክር አገልግሎትን ለማገዝ በተዘረጋው የ"8028" የስልክ መስመር ከ7 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች በነጻ በመደወል የምክር አገልግሎት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም 344 ከሚሆኑ የገበያ ማዕከላት በየጊዜው እየተሰበሰበና ትክክለኛነቱ እየተረጋገጠ የሚሰራጨው የገበያ መረጃ እስካሁን 2 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና ይበልጥ በማዘመን ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል።

በስትራቴጂው በከተማና በገጠር መካከል ያለውን የዲጂታል ልዩነት በማጥበብ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የሚሰራ ሲሆን፣ ለዚህም የዲጂታል መሰረተ-ልማትና የእውቀት ማሳደጊያ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ጠቁመዋል፡፡

በ2030 አርሶ አደሮችን ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኙበት ደረጃ ላይ ለማድረስ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ የቴክኖሎጂ አቅሞችን ተደራሽ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም