ቀጥታ፡

በዘንድሮ ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚስያችል ዝግጅት አድርገናል- ተማሪዎች

ቦንጋ፤ ሰኔ 18 /2018 (ኢዜአ)፦ በዘንድሮ ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን በቦንጋ ከተማ አስተዳደር አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተፈታኝ ተማሪዎች ገለጹ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ በበኩሉ በዘንድሮው ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና 17 ሺህ 458 ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀመጡ አስታውቋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተማሪዎች እንደገለፁት፤ በዘንድሮ ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል ዝግጅት አድርገናል።

በከተማው የቢሻው ወልደ ዮሐንስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎቹ ተማሪ ናታኔም ኤፍሬም እና ተማሪ ብሩክታዊት እሸቱ እንደተናገሩት በዘንድሮ ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት አድርገዋል።

ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 12ኛ ያለውን ይዘት ከመሸፈን ባለፈ ተጨማሪ የድጋፍ ትምህርቶችን በመከታተልና የፈተና ጥያቄዎችን በመስራት ራሳቸውን የማብቃትና የመለማመድ ስራ ትኩረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቱና መምህራን በቂ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን የተናገሩት ተማሪዎቹ ምሽቱን ጨምሮ ቤተ-መፃሐፍት እንዲጠቀሙ በማድረግና በስነ ልቦና ብቁ እንዲሆኑ እገዛዎች እንደተደረገላቸው ነው የገለጹት።

የቦንጋ መሃል ከተማ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆኑት ይንገስ ካሳሁንና ጨመረ መኮንን በበኩላቸው ዓመቱን ሙሉ በጥሩ ሁኔታ ትምህርታቸውን እንደተከታተሉ እና በቂ ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱን ገልፀዋል።

ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም በግላቸውም ፕሮግራም አውጥተው ሲያጠኑ መቆየታቸውን ጠቅሰው ይህም ጥሩ ወጤት ለማስመዝገብ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

ፈተናው በኦላይን የሚሰጥ በመሆኑ ለዚህ የሚሆን ክህሎት እንዲኖረን በተመቻቸው ኮምፒተር ልምምድ አድርገናል ያሉት ተማሪዎቹ በተረጋጋ መንፈስ ለመስራት የስነ-ልቦና ዝግጅት በማድረግ እየተጠባበቁ መሆናቸውን አብራርተዋል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ ደስታ ገነሜ (ዶ/ር) በክልሉ 17 ሺህ 458 ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተናውን እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

ከነዚህም ውስጥ 9 ሺህ 602ቱ በኦላይን (በበይነ መረብ) ፈተናቸውን እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ በተቃራኒ ፈረቃና ቅዳሜና እሁድ የድጋፍ ትምህርቶችን በመስጠት፣ የፈተና ጥያቄዎችን በማሰራት እንዲዘጋጁ መደረጉን ጠቁመዋል።

የዘንድሮ ሀገር አቀፍ ፈተና በክልሉ በ18 የፈተና ማዕከላት እንደሚሰጥ ጠቅሰው ለኦላይን ፈተና ኮምፒተሮችን እና ጄኔሬተሮችን የማዘጋጀት፣ የኢንተርኔት አቅምን የማሳደግና ሌሎች በቂ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም