መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል
ደሴ፤ ሰኔ 18/2018(ኢዜአ)፡- መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተቋማትን አገልግሎት በማዘመን ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ማስቻሉን የወልድያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ ገለፁ።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፣መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል።
አገልግሎቱ ዘመናዊ፣ፈጣን እና ቀልጣፋ መሆኑ የተገልጋዩን እንግልት ከማስቀረቱ ባሻገር ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መሆኑንም አስረድተዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ መስኮች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ሰፊ እድል የፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።
የወልድያ ከተማ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የቴክኖሎጅ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ምስጋናው ወርቅዬ በበኩላቸው፣ በማዕከሉ 13 የከተማ አስተዳደሩና የፌዴራል ተቋማት 102 አገልግሎቶችን እየተሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።
ተቋማቱ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በቅንጅት አገልግሎት በመስጠታቸውም ተገልጋዩ ህብረተሰብ በአንድ ቦታ እና በአጭር ጊዜ በመስተናገዱ እርካታን እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
በማዕከሉ የሁሉ አገልግሎት ባለሙያ አቶ ጥላሁን አስቻለሁ በበኩላቸው፣ ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ተገልጋዮች አስቀድሞ መረጃ በመስጠት በቀላሉ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
አገልግሎቱን በማግኝት ላይ የነበሩት የወልድያ ከተማ ነዋሪ ያልጋ ጌታሁን እንዳሉት፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ስራ መጀመሩ ከእንግልትና ከአላስፈላጊ ወጭ አድኖናል ነው የሚሉት።
ቀደም ሲል ጉዳዮቻችን ለማስፈፀም የሚኬድባቸው ቦታዎች አድካሚና ረጅም ጊዜ የሚወስዱ ከመሆኑም በላይ ለእንግልት የሚዳርጉ እንደነበርም አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን በማእከሉ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት እንደቻሉ ነው የተናገሩት።