ኮትዲቯር ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ከኩራሳኦ ጋር ትጫወታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኮትዲቯር ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ከኩራሳኦ ጋር ትጫወታለች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ):- በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የምድብ አምስት መርሐ ግብር ኮትዲቯር ከኩራሳኦ ጋር ጨዋታዋን ታከናውናለች።
ጨዋታው ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በፊላደልፊያ ስታዲየም ይካሄዳል።
ከሁለት ጨዋታዎች ሶስት ነጥብ ያገኘችው ኮትዲቯር ማሸነፍ ቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ያስገባታል። አቻ መውጣት በምርጥ ሶስተኝነት ሊያሳልፋት ይችላል።
በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን እያደረገች የምትገኘው ኩራሳኦ በአንድ ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ኩራሳኦ ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ያላት ብቸኛ እድል ማሸነፍ ብቻ ነው።
በዚሁ ምድብ ኢኳዶር ከጀርመን በኒው ዮርክ ኒው ጀርሲ ስታዲየም ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አኳዶር በአንድ ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች።
የአራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ጀርመን በስድስት ነጥብ ጥሎ ማለፍ መግባቷን አረጋግጣለች።
የደቡብ አሜሪካዋ ኢኳዶር ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት ተስፋውን ለማለምለም ጨዋታውን ማሸነፍ ይጠበቅባታል።
በተያያዘም በምድብ ስድስት የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ቱኒዚያ ከኔዘርላንድስ ከሌሊቱ ስምንት ላይ በካንሳስ ሲቲ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
በምድቡ ሁለት ጨዋታዎች የተሸነፈችው እና ከውድድሩ የተሰናበተችው ቱኒዚያ የመርሐ ግብር ማሟያ ጨዋታዋን ታደርጋለች።
በአራት ነጥብ ምድቡን የምትመራው ኔዘርላንድስ ካሸነፈች ወይም አቻ ከወጣች ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቷን ታረጋግጣለች።
በዚሁ ምድብ ጃፓን ከስዊድን ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ በዳላስ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ጃፓን በአራት ነጥብ ሁለተኛ፣ ስዊድን በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ጃፓን ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ወደ ቀጣዩ ዙር ያሳልፋታል።
በአንጻሩ ስዊድን ካሸነፈች በቀጥታ ወደ ቀጣዩ ዙር ታልፋለች። አቻ መውጣትም በምርጥ ሶስተኝነት ሊያሳልፋት ይችላል።
በምድብ አራት በተመሳሳይ ሁለት ጨዋታዎች ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ ይደረጋሉ።
ቱርኪዬ ከአሜሪካ በሎስ አንጀለስ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በምድቡ በሁለት ጨዋታ የተሸነፈችው ቱርኪዬ ከውድደሩ መሰናበቷ ይታወቃል።
በአንጻሩ ከአዘጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው አሜሪካ በስድስት ነጥብ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።
በሌላኛው የምድቡ መርሐ ግብር ፓራጓይ ከአውስትራሊያ በሳን ፍራንሲስኮ ቤይ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አውስትራሊያ እና ፓራጓይ በተመሳሳይ ሶስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ማሸነፍ ሀገራቱን ወደ ጥሎ ማለፉ ያስገባቸዋል። አቻ መውጣት አውስትራሊያን በቀጥታ ወደ ቀጣዩ ዙር እንድታልፍ ያስችላታል።
ፓራጓይ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ካገኘች በምርጥ ሶስተኝነት የማለፍ እድል ይኖራታል።