በኦሮሚያ ክልል የተከናወኑ የመስኖ ልማት ሥራዎች ዜጎችን ከተረጂነት አውጥተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የተከናወኑ የመስኖ ልማት ሥራዎች ዜጎችን ከተረጂነት አውጥተዋል
ሮቤ፣ሰኔ 18/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል የአርሶና አርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስ የተከናወኑ የመስኖ ልማት ሥራዎች ዜጎችን ከተረጂነት በማውጣት ራሳቸውን እንዲችሉ ዕድል መፍጠሩን የክልሉ የመስኖ ልማትና አርብቶ አደር ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊና የአርብቶ አደር ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሮባ ቱርቼ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአርሶና አርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስና የኑሮ ሁኔታወን ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በክልሉ በለውጡ ዓመታት የሕዝቡን የድርቅ ተጋላጭነት የመቋቋም አቅም ለማሳደግ ከተሰሩት ሥራዎች መካከል የመስኖ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራዎች አንዱ ነው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና አርሶና አርብቶ አደሩ በዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ እንዳይሆን ለማድረግ ለመስኖ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በ2018 የበጀት ዓመት ብቻ የአርብቶ አደሩንና የከፊል አርብቶ አደሩን የድርቅና አደጋ መቋቋም አቅም የሚያሳድጉ 256 የሚሆኑ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው ከተገነቡት የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል 56 በመቶው የሚገኙት በአርብቶ አደር አካባቢዎች ነው ብለዋል።
በተለይም 'ፊና' በተሰኘ ፕሮግራም አማካኝነት ወደ ግንባታ ከገቡ 73 የመስኖ ግድቦች መካከል 38ቱ ተጠናቀው በአሁኑ ወቅት 78 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ለሰውና ለእንስሳት መጠጥ የሚውል ውኃ የመያዝ አቅም መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
አቶ ሮባ እንዳሉት፣ የክልሉ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ባለፉት አምስት ዓመታት አንድ ሺህ የሚሆኑ ትላልቅ፣ መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በክልሉ ቀደም ሲል ከ70 ሺህ ሄክታር የማይበልጠው በመስኖ የሚለማው መሬት በአሁኑ ወቅት ወደ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር ማሳደግ ተችሏል።
የልማት ፕሮጀክቶቹ በተለይ በቆላማ የክልሉ አካባቢዎች እውን መሆን ቀደም ሲል በሴፍቲኔት ዕርዳታ ይተዳደሩ የነበሩ ዜጎችን በመስኖ አማራጭ በመሳተፍ ራሳቸውን እንዲችሉ ዕድል መፍጠሩን የባሌና ምስራቅ ባሌ ዞን አርብቶ አደሮችን በማሳያነት አንስተዋል።
በተጨማሪም በእነዚህ አካባቢዎች በተሰሩ ግድቦች የተከማቸ ውሃ ለሰውና ለእንስሳት መጠጥ ከማገልገሉ ባለፈ፣ አርብቶ አደሩ በአሳ እርባታ ስራ ተሰማርቶ አዲስና አማራጭ የገቢ ማግኘት መጀመሩንም ገልጸዋል።
የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው እንዳሉት ፤ በዞኑ የአርሶና አርብቶ አደሩ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ የዝናብና ሌሎች የውኃ አማራጮች በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በትኩረት እየተሠራ ነው።
በዞኑ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ከ500 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በመኽር እርሻ ብቻ በዝናብ እንደሚለማ ጠቁመዋል።
እንዲሁም የተለያዩ የመስኖ አማራጮችን በመጠቀም ከ170 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ እየለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ትኩረት አግኝተው ሲሠራባቸው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በዞኑ የደሎ መና ወረዳ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት የዌልመልና ያዶት የመስኖ ፕሮጀክቶች የአርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት በመቀነስ ሕይወቱ እንዲሻሻል እያገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይ የፕሮጀክቶቹ ወደ ሥራ መግባት ከዚህ በፊት በሴፍቲኔት ጠባቂነት የሚታወቁ የአካባቢው አርብቶ አደሮች ከመስኖ እርሻ ጋር በመተዋወቅ የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ እያገዘ መምጣቱንም አክለዋል።