ሞሮኮ እና ደቡብ አፍሪካ ወደ ጥሎ ማለፍ ተሸጋግረዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሞሮኮ እና ደቡብ አፍሪካ ወደ ጥሎ ማለፍ ተሸጋግረዋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የምድብ አንድ እና ሶስት የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ከእኩለ ሌሊት በኋላ ተደርገዋል።
በአትላንታ ስታዲየም በተካሄደው የምድብ ሶስት ጨዋታ ሞሮኮ ሃይቲን ከመመራት ተነስታ 4 ለ 2 አሸንፋለች።
አሽራፍ ሀኪሚ፣ እስማኤል ሳይባሪ፣ ሶፊያን ራህሚ እና ጌሲም ያሲን ግቦቹን አስቆጥረዋል።
እስማኤል ሳይባሪ በውድድሩ ላይ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ሶስት አድርሷል።
ዊልሰን ኢሲዶር እና የሞሮኮው ግብ ጠባቂ ያሲን ቦኖ በራሱ ላይ የሃይቲን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ሞሮኮ በሰባት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ጥሎ ማለፍ ገብታለች።
ሞሮኮ በዓለም ዋንጫው ታሪክ ግማሽ ፍጻሜ የገባች የመጀመሪያ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗ ይታወቃል።
አስቀድማ ከውድድሩ የተሰናበተችው ሀይቲ ያለ ምንም ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።
በሚያሚ ስታዲየም በተካሄደው የምድብ ሶስት ሌላኛው መርሐ ግብር ብራዚል ስኮትላንድን 3 ለ 0 አሸንፋለች።
ሺኒሸስ ጁኒየር ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ማትያስ ኩንሃ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ቪኒሸስ ጁኒየር በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት አራት አድርሷል።
በጉዳት ላይ የነበረው ኔይማር ተቀይሮ በመግባት የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ጨዋታውን አድርጓል።
ውጤቱን ተከትሎ ብራዚል በሰባት ነጥብ የምድቡ መሪ በመሆን ጥሎ ማለፍ ገብታለች።
ስኮትላንድ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች ሲሆን ምርጥ ሶስተኛ ሆና ለማለፍ የሌሎች ምድቦችን ውጤት ትጠብቃለች።
በተያዘዘም በምድብ አንድ የምትገኘው ደቡብ አፍሪካ ኮሪያ ሪፐብሊክን 1 ለ 0 አሸንፋለች።
በሞንቴሬይ ስታዲየም በተካሄደው ታፔሎ ማሴኮ በ63ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።
ድሉን ተከትሎ ደቡብ አፍሪካ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጥሎ ማለፉ አልፋለች።
ኮሪያ ሪፐብሊክ በሶስት ነጥብ ሶሶተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ምርጥ ሶስተኛ ሆኖ ለማለፍ የሌሎቹን ምድቦች ውጤት ትጠብቃለች።
በዚሁ ምድብ በሜክሲኮ ሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሜክሲኮ ቼክ ሪፐብሊክን 3 ለ 0 አሸንፋለች።
ማቲዮ ቻቬዝ፣ ጁሊያን ኪኖኔስ እና አልቫሮ ፊዳልጎ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
አስቀድማ ወደ ጥሎ ማለፉ መግባቷን ያረጋገጠችው ሜክሲኮ በዘጠኝ ነጥብ የምድቡ መሪ ሆና አጠናቃለች።
በዓለም ዋንጫው ሁሉንም የምድቧን ጨዋታ ያሸነፈች ብቸኛ ሀገር ሆናለች።
ሜክሲኮ ከዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ ናት።