ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚቀርቡት ስምንቱ አጀንዳዎች ከኢትዮጵያ ህዝብ የተቀዱ ናቸው - ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚቀርቡት ስምንቱ አጀንዳዎች ከኢትዮጵያ ህዝብ የተቀዱ ናቸው - ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚቀርቡት ስምንቱ አጀንዳዎች ከኢትዮጵያ ህዝብ ድምፅ፣ ቅሬታ፣ ፍላጎት፣ ተስፋና ስጋት የተቀዱ ናቸው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አስታወቁ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላለፉት አራት ዓመታት በመላው ኢትዮጵያና ከሀገር ውጭ ጭምር በመንቀሳቀስ፣ ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ዜጎችን በማማከርና በማወያየት የሰበሰባቸውንና ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ግብአት የሚሆኑ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን ይፋ አድርጓል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ዘላቂ ሰላም፣ ሀገራዊ መግባባት እና የጋራ እጣ ፈንታን በጋራ መበየን እጅግ አስፈላጊ በሆነበት ታሪካዊ መንገድ ላይ ትገኛለች።
ኮሚሽኑ ይህንን ታሪካዊ ጥሪ ለመመለስ በማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265/2014 በተሰጠው ስልጣን መሰረት፣ የህዝብን ቀጥተኛ ተሳትፎ ያረጋገጠና "ከታች ወደ ላይ" የሚለውን ስልት የተከተለ አካታችና ሁሉን አቀፍ ስራ ማከናወኑን አስታውቀዋል።
ይፋ የተደረጉት ስምንት ሀገራዊ አጀንዳዎች ሙሉ በሙሉ ከራሱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ድምፅ፣ ቅሬታ፣ ፍላጎት፣ ተስፋና ስጋት የተቀዱ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ሂደቱ ተአማኒና ሁሉንም ማህበረሰብ ያካተተ እንዲሆን ለማድረግም በሁሉም ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ሰፊ የህዝብ ምክክር መካሄዱን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የፌዴራል ተቋማት አመለካከታቸውን ያበረከቱ ሲሆን፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላትም በሂደቱ ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ በማድረግ ድምፃቸው እንዲካተት ተደርጓል ብለዋል።
ኮሚሽኑ ለግለሰቦች፣ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ለፖለቲካ ፓርቲዎች በሩን ክፍት በማድረግ ግብዓቶችን መሰብሰቡን ጠቅሰዋል፡፡
ይህም የህዝብን ተሳትፎ ማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገራዊ ችግሮች መፍትሄ ማምጣት እንደሚችል መልዕክት ያስተላለፈ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በጥንቃቄ የታዩት እነዚህ ግብዓቶች በኢሜል፣ በፖስታ፣ በስልክ፣ በማህበራዊ ሚዲያና በአካል በመገኘት የተሰበሰቡ ሲሆን፣ ሂደቱን ይበልጥ ለማጠናከር የአካዳሚክና የፖሊሲ ጥናት ግኝቶችም በጥልቀት ጥቅም ላይ ውለዋል ነው ያሉት።
የአጀንዳዎቹ ልየታና ቀረጻ ሂደቱ ግልጽና ስርዓቱን የተከተለ እንደነበር የገለጹት ፕሮፌሰር መስፍን፣ ሂደቱ ሶስት ዋና ዋና ደረጃዎችን ያለፈ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ግብዓቶችን የመሰብሰብ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የአጀንዳ ቀረጻ የአሰራር ስርዓት በመቅረጽ፣ ጉዳዮችን በየፈርጁ የማደራጀት፣ የማጠናከርና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የመለየት ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ እጅግ መሰረታዊና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን መስፈርቶች መሰረት በማድረግ በኮሚሽኑ ምክር ቤት ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ በሀገር ደረጃ ምክክር የሚደረግባቸውና የማይደረግባቸው ተለይተው መጣራታቸውንም ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑ ሀገራዊ ተብለው በተለዩት አጀንዳዎች ዙሪያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማድረግ፣ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የሚቀርቡት ስምንት አጀንዳዎችን ለህዝብ ይፋ አድርገዋል፡፡
ለዋናው ሀገራዊ ምክክሩ የሚቀርቡ ስምንቱ ዋና ዋና አጀንዳዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. የሀገር ግንባታ
2. የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ እንዲሁም የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት
3. የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ
4. የሃይማኖት ጉዳዮች
5. የተቋማት ግንባታ፣ የህግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች
6. ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች
7. ሙስናና መልካም አስተዳደር
8. ሰላም ግንባታ ናቸው።
እነዚህ አጀንዳዎች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ከውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (ዲያስፖራ) እስከ ሲቪል ማህበረሰብ፣ እንዲሁም ከፌደራል ተቋማት እስከ ክልል መንግስታት ድረስ በተካሄዱ ሰፊ፣ አካታችና ግልጽ የሆኑ ሂደቶች የተዘጋጁ መሆናቸውን ፕሮፌሰር መስፍን አብራርተዋል።
የምክክሩ ስኬት የሁሉንም ዜጋ በጎ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በሂደቱ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ በኮሚሽኑ ስም ጥሪ አቅርበዋል።
ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በተለይም ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት የሚከተሉትን የተናጠል የስራ መመሪያና ጥሪ አስተላልፈዋል፦
ከ130 ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን የሀገሪቱን ህዝብ ወክለው በሂደቱ ላይ የሚሳተፉ የህዝብ ወኪሎች እነዚህን የተዘጋጁ አጀንዳዎች በትልቅ ትኩረት እንዲያጠኑና እንዲመረምሩ አሳስበዋል።
ወኪሎቹ በሚቀጥለው የምክክር ሂደት ውስጥ የወከሉትን ህዝብ እውነተኛ ሀሳብ በግልጽ ማሰማትና ለሀገራዊ መግባባት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከራሳቸው የፓርቲ ጥቅም በላቀ ሁኔታ በመቆም፣ ለሀገራዊ መግባባቱ መሳካት የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉና ድምፃቸው በቀላሉ የማይሰማ የተገለሉ ቡድኖችን ድምፅ በትጋት እንዲያሰሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የሃይማኖት ተቋማት የኢትዮጵያን ነባር የምክክርና የእርቅ ባህል በጽኑ እንዲደግፉና እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።
ወጣቶችና ሴቶችም ለምክክሩ ትኩረት በመስጠት በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን የቀረቡት አጀንዳዎች ሀገሪቱን ወደ ልማትና ሰላም የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን በሚያሳይ መልኩ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስ እንዳለባቸው ፕሮፌሰር መስፍን አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።