ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ በማድረግ ተወዳዳሪ የሰው ሀይል እያፈራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ በማድረግ ተወዳዳሪ የሰው ሀይል እያፈራ ነው
ሰመራ፣ሰኔ 17/2018(ኢዜአ):- ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ በማድረግ ተወዳዳሪ የሰው ሀይል እያፈራ መሆኑን ገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው በመደበኛና ተከታታይ መርሀ ግብር በመጀሪያ ዲግሪና በድህረ ምረቃ ያስለጠናቸውን 392 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት መሐመድ ኡስማን (ዶ/ር) በምረቃ ሰነ ሰርዓቱ ላይ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ በማድረግ ተወዳዳሪ የሰው ሀይል እያፈራ ነው።
ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ለማድረግም ዲጂታላይዜሽን አሰራር መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።
ከመማር ማስተማሩ በተጓዳኝም ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ኑሮ መሻሻል የሚያግዙ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው ይህም ለአርብቶ አደሩ አካባቢዎች መሻሻል አዎንታዊ ለውጦች እንዲመጡ አግዟል ብለዋል።
ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት በሚሰማሩበት የስራ መስክ በመተግበር የራሳቸውንና የህብረተሰቡን ኑሮ ለመቀየር መትጋት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ።
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በእውቀት የበቃ ዜጋን ለማፍራት በሰው ሀይል ልማትና በግብአት መደራጀቱን አንስተዋል።
በዚህም የምረቃ ፕሮግራሞቹን በማስፋት፣ በቅድመና ድህረ ምረቃ ትምህርት ሀገሪቱ የምትፈልገውን የሰው ሀይል እያፈራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የትምህርት ይዘቱንም ከገበያ ፍላጎት ጋር በማጣጣም በኢንዱስትሪ እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ አበክሮ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።