ቀጥታ፡

የጤና ሥርዓቱን ለማጠናከር በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የውሳኔ አሰጣጥ እየተገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦ የጤና ሥርዓቱን በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የውሳኔ አሰጣጥ በሚያስችል መልኩ ለመገንባት ጠንካራ አመራር እየተሰጠ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር "ከማስረጃ ወደ ተግባር፤ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የጤና ስርዓትን መገንባት" በሚል መሪ ሐሳብ የመጀመሪያውን አገር አቀፍ በማስረጃ የተመሰረተ ውሳኔ አሰጣጥ ጉባኤ ማካሄድ ጀምሯል።


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት፤ ሚኒስቴሩ የጤና ፖሊሲውን በመቀየር መከላከልና አክሞ ማዳንን ማስቀመጡን አስታውሰዋል።

እነዚህን የመከላከልና የአክሞ ማዳን ተግባራትን የሚያግዙ ፖሊሲዎች በስትራቴጂ፣ በመዋቅር፣ በአፈጻጸም እንዲሁም በአካሄድ ረገድ በስኬታማነት እንዲፈጸሙ ከየአቅጣጫው የሚመጡ መረጃዎች ለጤናው ዘርፍ ዋነኛ መደገፊያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የምንጠቀምባቸው መረጃዎች የሀገራችንን ሉዓላዊነት መጠበቂያና በራሳችን እቅድ የራሳችንን የምንሰራበት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

መረጃዎች ሀገርና ህዝብን የሚደግፉ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በመሆኑም ለፖሊሲ፣ ለአገልግሎትና ለአቅጣጫ መቀየሪያ የሚሆኑ ጠቃሚ መረጃዎችን በጋራ ለማውጣት ሁሉም በትኩረት እንዲሰራ ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በላይ ካሳ በበኩላቸው፤ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አሰጣጥ አመራርን እንደሚያጠናክርና መሪዎች ከአማራጮች መካከል ይበልጥ በግልጽነት እንዲመርጡ ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡

ጉባኤው ማስረጃ ጠቃሚ መሆኑን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ማስረጃን ወደ ተግባር የሚቀይሩ ተቋማትን በመገንባት ጭምር የሚታወስ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ለሁለት ቀናት የሚቆየው አገር አቀፍ ጉባኤ፤ በተለያዩ የምርምር ሥራዎች አቀራረብ፣ በፓናል ውይይቶችና በቀጣይ አቅጣጫዎች አመላካች ውሳኔዎች እንደሚጠናቀቅ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም