በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለመምህራን ልማት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለመምህራን ልማት ትኩረት ተሰጥቷል
አርባ ምንጭ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ):-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ለመምህራን ልማት ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው "በቅቶ ማብቃት ልቆ ማላቅ" በሚል መሪ ሃሳብ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራን የአሠልጣኞች ስልጠና በአርባምንጭ ከተማ እየሰጠ ነው።
የቢሮ ሃላፊው አብዮት ደምሴ ስልጠናው ዛሬ ሲጀመር እንደገለጹት በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሰው ሀይል ልማትና ግብአት አቅርቦት ላይ ትኩረት ተሰጥቷል።
ለዚህም ሀገር አቀፍ የትምህርት ፍኖተ ካርታውን በመተግበር የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ይበልጥ ለመስራት የመምህራን አቅም ማጎልበት ላይ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
ዛሬ የተጀመረው የመምህራን የአሠልጣኞች ስልጠናም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
ስልጠናው የቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራንን አቅም በማጎልበት ህጻናትን በአሳታፊ ዘዴ እና በተግባራዊ እንቅስቃሴዎች የማስተማር ክህሎትን ለማዳበር አጋዥ መሆኑን አስታውቀዋል ።
የቢሮው ምክትልና የመምህራን ትምህርት አመራር ልማት ዘርፍ ሃላፊ ታምራት ይገዙ (ዶ/ር) በበኩላቸው ትምህርት ለሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት መሰረት በመሆኑ ዘርፉን በእውቀት መምራት ይገባል ብለዋል ።
ለዚህም የቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራን የሙያ ብቃት ማጎልበቻ እና የደረጃ ማሟያ ስልጠና በየጊዜው ከመስጠትም በላይ መምህራን የትምህርት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ስልጠናው በቅቶ የሚያበቃና ልቆ የሚያልቅ መምህራንን በማፍራት ብቁ ትውልድ ለመገንባት ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ የአርባምንጭ ትምህርት ኮሌጅ ዲን እንግዳ እንድሪያስ (ዶ/ር) ናቸው።
የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የህፃናትን የመማር ፍላጎት፣ ክህሎትና ስብዕና መሠረት አድርጎ መስራት አስገዳጅ መሆኑን አስረድተዋል ።
ለዚህም ለአመቻች መምህራን የሙያ ብቃትን ማሳደግና ግብአትን ማሟላትን ይጠይቃል ብለዋል።
የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ሀገርና ትውልድ ለመገንባት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መጠናከር እንደሚገባውም አክለዋል።