7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝቡን ወሳኝነት በግልጽ አረጋግጧል - የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝቡን ወሳኝነት በግልጽ አረጋግጧል - የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፡- ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝቡን ወሳኝነት በግልጽ ያረጋገጠና ለሁሉም አካላት ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ነው ሲል የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ ብልጽግና ፓርቲ አብላጫውን የሕዝብ ድምጽ አግኝቶ ማሸነፉን ተከትሎ የእንኳን ደስ አላችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፏል።
በመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቱም፤ የክልላችንንና የሀገራችንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ በትብብር፣ በፉክክርና በአንድነት መርኅ ላይ በመንተራስ ከመንግሥት እና ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ ስሠራ ቆይቻለሁ ብሏል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫም በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩሉን መሥራቱን ጠቁሞ፤ የፓርቲዎቻችንን ፕሮግራም በተለያዩ አመራጮች ለሕዝብ በማቅረብ ለመወዳደር የቻልንበት ጊዜ ነበር ነው ያለው፡፡
አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንዲሆን የሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ርብርብ ከፍተኛ እንደነበር አውስቶ፤ የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላትም ውጤቱን ተቀብለው ለሕዝቡ ውሳኔም ተገዥ መሆናቸውን ለኢዜአ በላከው መረጃ አረጋግጧል።
በዚህም መሠረት፤ ምርጫው በሰላም ተጠናቆ ሀገራችን ስላሸነፈች ለመላው ሕዝባችን እንኳን ደስ አላቸሁ ለማለት እንወዳለን ብሏል የጋራ ምክር ቤቱ።
የምርጫው ሂደትና ውጤቱም ዴሞከራሲያዊና የሕዝብን ወሳኝነት ያረጋገጠ በመሆኑ የሕዝቡን ድምጽ በጸጋ እንቀበላለን ሲልም አስታውቋል።
በዚህ ታሪካዊ የምርጫ ሂደት ውስጥ ለተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ለሁሉም ባለድርሻ አካላትም ምክር ቤቱ ምሥጋና አቅርቧል።
በመጨረሻም ብልጽግና ፓርቲ አብላጫውን የሕዝብ ድምጽ አግኝቶ ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባረጋገጠው መሠረት፤ የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለብልጽግና ፓርቲ እንኳን ደስ አላችሁ እያልን በቀጣይ ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ነን ሲል አረጋግጧል።
በአጠቃላይ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝቡን ወሳኝነት በግልጽ ያረጋገጠና ለሁሉም አካላት ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ መሆኑንም ነው ያስታወቀው።
በተጨማሪም ለሀገራችን የዴሞከራሲ ምኅዳር መስፋት ዐሻራ ጥሎ ያለፈ በመሆኑ፤ ሁሉም አካላት ይህንን ጅምር ሂደት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ መሥራትና ከምርጫ ማግስት ጀምሮ ፊታችንን ወደ ልማትና ሰላም ግንባታ በማዞር በሁሉም ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት መትጋት ይኖርብናል ነው ያለው፡፡
ብልጽግና ፓርቲም ሕዝቡ የሰጠውን አደራ በጥንቃቄ በመያዝ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሌት ተቀን ተግቶ እንዲሠራ ጠይቋል።