ቀጥታ፡

ረቂቅ አዋጁ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት የሚደግፍ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡   

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ይፋዊ የሕዝብ መድረክ አካሂዷል፡፡  

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በዚሁ ወቅት፤ በሕዝብ መድረኩ ለተሳተፉ አካላት ስለ ብሔራዊ የካርበን ግብይት ረቂቅ አዋጁ ይዘትና አስፈላጊነት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡


 

በማብራሪያቸው፤ የካርበን ግብይት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የተዘረጋ ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት መሆኑን ጠቅሰው ዓላማውም ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ መጠን ማስወገድ፣ መቀነስ እና መከላከል ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ለመተግበር በፖሊሲ የተደገፈ ተግባር እያከናወነች እንደምትገኝም ጠቁመው ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ማስገኘት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ለሕዝብ ውይይት ይፋ የተደረገው ረቂቅ አዋጅ በሀገራችን የካርበን ገበያ ልማት ላይ ወሳኝ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ጠቅሰው የካርቦን ግብይት ኢትዮጵያ ከዘርፉ ተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭ የምታገኝበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የበካይ ጋዝ የልቀት መጠን እንዲቀንስ በማድረግ የአረንጓዴ እና የዘላቂ ልማት ግቦች እንዲሳኩ እንደሚያደርግም እንዲሁ፡፡

በሕዝብ መድረኩ የተሳተፉት የአረንጓዴ ዐሻራ ቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፤ ረቂቅ አዋጁ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የሰጠችውን ትኩረት በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅ የካርበን ግብይት ለሀገራችን እንደ አንድ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት አማራጭ ሆኖ ስለሚያገለግል ሂደቱ በተፋጠነ መልኩ ወደ ተግባር መግባት እንዳለበት አመላክተዋል፡፡


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጀ፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶችን ከፈረሙ ሀገራት አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።

ይህ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅ የተበታተኑ አሠራሮችን ወደ አንድ በማምጣት፣ የካርበን ግብይትን በተሟላ እና ግልጽ በሆነ የሕግ ማዕቀፍ ለመምራት ያስችላል ብለዋል።

ረቂቅ አዋጁ ሀገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት የሚደግፍና ለተግባራዊነቱ ትልቅ መሠረት የሚጥል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም አረንጓዴ ልማትን እና የታዳሽ ኃይል አጠቃቀምን የሚያበረታታ በመሆኑ፣ ሀገራችን ከምታመነጨው የካርቦን ልቀት ገቢ እንድታገኝ ያደርጋታል ብለዋል።

ይህ ወሳኝ ሰነድ ጸድቆ ወደ ተግባር ሲገባ የኢትዮጵያ የካርበን ግብይት ግልጽ መመሪያና ሥርዓት እንዲኖረው ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።

በመሆኑም አዋጁ አስፈላጊዎቹን የዝግጅት ሒደቶች በሙሉ አልፎ ለትግበራ እንዲበቃ ቋሚ ኮሚቴው የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም