በዞኑ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው
ጊምቢ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ወለጋ ዞን የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆናቸውን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።
በምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ ግንባታቸው የተጠናቀቁ የተለያዩ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።
በወቅቱም የኦሮሚያ ክልል የመንገድ እና ሎጂስቲክስ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታዬ ጉዲሳ በክልሉ ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ ናቸው።
መሰረተ ልማቱም በአጭር እና በረጅም ጊዜ እቅድ የተገነቡ መሆኑንና በህዝቡና በአጋር አካላት ተሳትፎ መከናወናቸውን ጠቅሰው ተግባራቱም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የክልሉ መንግስት የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ባለው ቁርጠኝነት በርካታ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ያነሱት ኃላፊው ዛሬ በዞኑ የተመረቁት ፕሮጀክቶችም የዚሁ ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፈ በበኩላቸው በዞኑ ለነዋሪዎች የመሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ግንባታዎች በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ ተገንብተው ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የዚሁ አካል የሆኑትና በበጀት ዓመቱ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም በዞኑ የህዝቡን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።