ቀጥታ፡

በተደመረ አቅም የግብርና ምርታማነትን በማስፋትና በማሳደግ ከተረጂነት የመውጣት ጥረት በልዩ ትኩረት እየተሰራበት ነው- ርእሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ዱራሜ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦ በተደመረ አቅም የግብርና ምርታማነትን በማስፋትና በማሳደግ ከተረጂነት የመውጣት ጥረት በልዩ ትኩረት እየተሰራበት መሆኑን የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።

"የተቀናጀ የግብርና ትጋት ለላቀ ምርታማነት" በሚል መሪ ሀሳብ የመኸር ወቅት የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራዎች የንቅናቄ መድረክ በዱራሜ ከተማ ተካሄዷል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ ከተረጂነት ለመውጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዙ የግብርናው ዘርፍ የልማት ስራዎች ይጠናከራሉ።

በክልሉ በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ በሚገኙ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም የማህበረሰቡ ተጠቃሚነት እያደገ ስለመምጣቱም አስረድተዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ትግበራም የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ተግባሩን ማላቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው በክልሉ በ2018/19 የመኸር ወቅት 800 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ ማሳ ይለማል ብለዋል።


 

በዚህም 70 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለማምረት ግብ ተቀምጦ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።

ክልሉ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እያከናወናቸው በሚገኙ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይም የአካባቢን ፀጋ ለይቶ በማልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው እሳቤ እውን በማድረግ የማህበረሰቡ ተጠቃሚነት እያደገ ስለመምጣቱም ጠቁመዋል።

በዚህም አርሶ አደሩ ከቤት ፍጆታው አልፎ ለገበያና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ማምረት ስለመጀመሩና ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የንቅናቄ መድረኩ በመኸር ወቅት የታቀደውን ግብ ለማሳካት የጋራ ተግባቦት ለመፍጠር እንደሚያግዝና አመራሩና የግብርና ባለሙያው ለእቅዱ መሳካት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ በበኩላቸው በዞኑ የመኸር ወቅት የግብርና ልማት 47 ሺህ ሄክታር ማሳ ስንዴንና ገብስን ጨምሮ በሌሎች ዋና ዋና ሰብሎች ይለማል ብለዋል።

በዞኑ የኩታ ገጠም እርሻ ትግበራ ለምርታማነት ማደግ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቅሰው በመኸር ወቅት የግብርና ልማትም ስነ-ዘዴው በትኩረት ተግባራዊ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም