ቀጥታ፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ ችግሮችን እየፈታ ነው

ጊምቢ፡ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ወለጋ ዞን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መረዳዳትን በማጠናከር ማህበራዊ ችግሮችን እየፈታ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

በምዕራብ ወለጋ ዞን የዘንድሮ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በቆንዳ ወረዳ የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤት በማደስ ተጀምሯል።




 የዞኑ አስተዳደሪ አቶ ተሊላ ተረፈ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ በዞኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህዝቡን የመረዳዳት ባህልና እሴት በማጠናከር ማህበራዊ ችግሮችን እየፈታ ነው።
 
ወጣቶች ጊዜና ጉልበታቸውን በበጎ ፈቃድ ስራ ላይ ለማዋል ያሳዩት ተነሳሽነት የዞኑ ልማት ለማፋጠን እያገዘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
 
ይህንን በጎ ተግባር በተጠናከረ መልኩ በማስቀጠል ለተቸገሩ ወገኖቻችን ልንደርስላቸው ይገባል ሲሉም አመልክተዋል። 

የምእራብ ወለጋ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በበኩላቸው በዞኑ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ላይ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

በአገልግሎቱም ከ800 ሺህ በላይ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ጠቁመዋል።
 
በዞኑ ከዚህ ቀደም በክረምት እና በበጋ ወራት  ወጣቶችን በማስተባበር እየተሰራ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውጤታማ እንደነበር ጠቁመው፤ በዚህም የበርካታ ወገኖች ችግር እየተቃለለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም