ቀጥታ፡

የሴቶች ማብቃትና የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት ፖሊሲ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ አለው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦ አዲሱ ብሔራዊ የሴቶች ማብቃትና የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት ፖሊሲ የሴቶችን ሁለንተናዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ከማጠናከር አንጻር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን ገለፁ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 55ኛ መደበኛ ስብሰባ ብሔራዊ የሴቶች ማብቃትና የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ረቂቅ ፖሊሲ ማፅደቁ ይታወሳል።

የፀደቀው ፖሊሲም ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃትን ለመከላከል እና ጥበቃና ምላሽ ለመስጠት፣ ልዩ ትኩረት ለሚሹ ሴት አካል ጉዳተኞች እና ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች ምላሽ ለመስጠት ፋይዳው የጎላ መሆኑ መገለፁ ይታወቃል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ብሔራዊ የሴቶች ማብቃት እና የስርዓተ ፆታ እኩልነት ፖሊሲን ወደ ተግባር ለማስገባት በፌዴራል ባሉ ተቋማቶች እንዲሁም በክልሎች ለሚገኙ የስራ ሃላፊዎች ለሶስት ቀናት የሚቆይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በየደረጃው ላሉ አመራሮች መስጠት ጀምሯል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን ስልጠናውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለፁት፤ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው ፖሊሲ ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ ባለመሆኑ አሁን ላይ ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ እንዲሻሻል መደረጉን አስረድተዋል።

አሁን የተሻሻለው ብሔራዊ የሴቶች ማብቃት እና የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት ፖሊሲ እነዚህን ችግሮች በመፍታት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በሚመጥን መልኩ ሴቶችን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል።

ፖሊሲው ስር ነቀል የሆኑ ጉዳዮች ላይ በቂ ትኩረት የሚሰጥ እንዲሁም ጥበቃና ምላሽ ለመስጠት እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ስርዓተ-ጾታን መሰረት ካደረጉ አለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶች ጋር የተጣጣመ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም