በክልሉ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን ተደራሽ የማድረግ ተግባር ይጠናከራል-ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን ተደራሽ የማድረግ ተግባር ይጠናከራል-ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)
ሚዛን አማን፣ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን ተደራሽ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በሚዛን አማን ከተማ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
የሚዛን አማን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የ5 ኪሎሜትር ኮሪደር ልማትና የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ መናኸሪያ ዛሬ ተመርቀዋል ።
ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማቶችን ማስፋፋትና ተደራሽ ማድረግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው።
በዚህ እንቅስቃሴ ውሰጥ የሕዝቡ ተሳትፎ እያደገ በመምጣቱ ትላልቅ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ለአገልግሎት ማዋል እየተቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የሚዛን አማን መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በቴክኖሎጂ ታግዞ ተቋማትን በማስተሳሰር ተገልጋዮችን ከብልሹ አሠራር የሚታደግ ነው ብለዋል።
መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው በሌሎች የክልሉ ከተሞችም ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ዛሬ ወደ አገልግሎት የገባው የሚዛን አማን መናኸሪያ የትራንስፖርት አገልግሎትን የሚያሳልጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኮሪደር ልማት ስራም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በዞኑ በመንግስትና በህዝብ ተሳትፎ የተከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለዚህም ለምረቃ የበቃውን የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ለአብነት ጠቅሰዋል ።
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ሌዊ በከተማው የተመረቁ ፕሮጀክቶች ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
የልማት ፕሮጀክቶቹ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከተማውን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል ።
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ያሲን የካ እና ወይዘሮ ጥሩዬ ከበደ በከተማው በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል ።