ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል የሆኮ ወረዳ ነዋሪዎች በአማራጭ የኃይል አቅርቦት ሥራዎች ተጠቃሚ ሆነዋል

ሀዋሳ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ):-በሲዳማ ክልል የሆኮ ወረዳ ነዋሪዎች በመንግስት በተከናወኑ አማራጭ የኃይል አቅርቦት ሥራዎች  ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናገሩ።

በወረዳው በሆዲ ቦኩ ከተማ ከፀሐይ ሀይል 525 ኪሎ ዋት የሚያመነጨው የሆዲ ቦኩ ሚኒ ግሪድ የፀሐይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።


 

መንግስት የኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት ባለተዳረሰባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የሶላር ሚኒ ግሪድ ሃይል ልማትን በማስፋፋት ዜጎች የአማራጭ ሀይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ ነው።

በሲዳማ ክልል የሆኮ ወረዳ ነዋሪዎችም በቅርቡ ተገንብቶ ለአገልግሎት በበቃው የሆዲ ቦኩ ሚኒ ግሪድ የፀሐይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል።  

ኢዜአ በሆኮ ወረዳ ሆዲ ቦኩ ከተማ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ አሸናፊ ሌንጅሶ እንዳሉት፣ በአካባቢው የኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት ባለመኖሩ ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገው ቆይተዋል።


 

በአሁኑ ወቅት በፀሐይ ሀይል የሚሰራ አማራጭ ሀይል ማግኘታቸው ኑሯቸውን ከማቅለሉ ባለፈ ማህበራዊ አገልግሎቶችንም በተሻለ ለማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

አማራጭ የሀይል አቅርቦት መኖሩ በጤና ተቋማት የሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት እንዲሻሻል ማድረጉንም ተናግረው፣  ህብረተሰቡ የሀይል ተጠቃሚ እንዲሆን መንግስት ለመኖሪያ ቤት ቆጣሪ በነጻ ማቅረቡንም ተናግረዋል።


 

ለዘመናት የነበረው የሀይል ጥያቄያቸው በመፈታቱ መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ጎሹ ጋኖሌ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።

በአካባቢያቸው የተገነባው የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ኑሯቸውን በማቃለል ጉልበትና ጊዜያቸውን ለሥራ በማዋል ሕይወታቸውን ለመለወጥ የተሻለ ዕድል እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል።

አካባቢው የሀይል ተጠቃሚ መሆኑ ለንግድ እንቅስቃሴም ሆነ የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን በራስ ፈጥሮ ለመስራት ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።


 

በሆዲ ቦኩ ከተማ የ9ኛ ክፍል ተማሪው ምንጬ ደምሴ በበኩሏ "በመብራት እጦት ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገን ቆይተናል፤ ይሁን እንጂ በቅርቡ በተመረቀው የፀሀይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከጨለማ ሕይወት ወጥተናል" ብላለች።

የሀይል አቅርቦቱ ተማሪው በአግባቡ እንዲማር፣ ህብረተሰቡም ዘመናዊ ህይወትን እንዲላመድ እና ለወጣቱም የሥራ ዕድል ፈጠራ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግራለች።


 

የሲዳማ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ከበደ ጋኖሌ በበኩላቸው  በክልሉ የሀይል ተደራሽነትን ለማስፋት በተሰሩ ሥራዎች የዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተፈቱ ነው።

ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ የክልሉ አካባቢዎችን በአማራጭ የሀይል አቅርቦት ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ ከተጀመሩ አምስት የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሁለቱ ተጠናቀዋል ብለዋል።

በእዚህም የህዝቡ የሀይል አቅርቦት ጥያቄ እየተመለሰ መምጣቱን ኢንጂነር ከበደ ገልጸው፣ "በሆኮ ወረዳ የተመረቀው የፀሐይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከ2ሺህ የሚበልጡ አባውራዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል" ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፕሮጀክት ፖርትፖሊዮ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክንፈ ነጋሽ በበኩላቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለእዚህም ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ውጭ በሆኑ አካባቢዎች አማራጭ የፀሐይ ሀይል በማስፋፋት ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በእዚህም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች 97 ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውንና 43 እንደተጠናቀቁ ገልጸዋል። 

በእነዚህ አካባቢዎች ዜጎች የሀይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የመኖሪያ ቤት ቆጣሪ በነጻ እየቀረበላቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ክንፈ፣  የዜጎችን የሀይል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች በቀጣይም ይጠናከራሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም