በክልሉ የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ለማጎልበት የሚያስችሉ የልማት ስራዎች በስፋት እየተተገበሩ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ለማጎልበት የሚያስችሉ የልማት ስራዎች በስፋት እየተተገበሩ ይገኛሉ
ሐረር ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግና ለማጎልበት የሚያስችሉ የኢንቨስትመንትና የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ኦርዲን በድሪ በሐረር ከተማ በግንባታ ላይ ያሉ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የሐረሪ ክልል በተለይም ጥንታዊቷ የጀጎል ግንብ የዓለም ቅርስነት ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ቀዳሚ ከሆኑ የባህልና የታሪክ ቱሪዝም መዳረሻዎች አንዷ ናት።
ከተማዋ ያላት ልዩ የእስልምና ታሪክ ቅርሶች፣ የሀረሪ ባህላዊ ቤቶች፣ የጅብ መመገብ ልማድ እንዲሁም የህዝቡ የአብሮነትና የሙዚቃ ባህል በየዓመቱ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን ይስባል።
የክልሉ መንግስትም በቅርብ ዓመታት ውስጥ በርካታ የሪፎርም እና የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ ሲሆን፥ በተለይም የቱሪዝም ዘርፉን በግል ባለሀብቱ ኢንቨስትመንት እገዛ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት የክልሉ መንግስት በኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ማበረታቻና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን አንስተዋል።
በክልሉ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በተደረገው የተቀናጀ ጥረትም አመርቂ ለውጥ መመዝገቡን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማው በግል ባለሀብቶች እየተገነቡ ያሉ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችም አበረታች ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፤ የግንባታ ስራዎቹም በታቀደላቸው የጊዜ ሰሌዳ እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የልማት ፕሮጀክቶቹ የክልሉን የቱሪዝም አቅም ለማሳደግና ለዜጎች የሚሆን የሥራ ዕድልን በስፋት ለመፍጠር ያላቸው ፋይዳም ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ተሰማርተው አበረታች አፈጻጸም እያሳዩ ላሉ ባለሀብቶች፣ የክልሉ መንግስት የሚያደርገውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።
ባለሀብቶቹም የጀመሩትን የግንባታ ስራ በፍጥነትና በጥራት አጠናቀው ለአገልግሎት ማብቃት እንዳለባቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ባካሄዱት በዚህ ምልከታ ላይ የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ አባላትን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች መታደማቸው ታውቋል።