ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አባወራዎች በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የሶላር ፓኔል ተሰራጭቷል

አዳማ ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አባወራዎች በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የሶላር ፓኔል ስርጭት መከናወኑን የክልሉ ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ገለጸ።

በቢሮው የኢነርጂ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ሶሬሳ እንደገለጹት፤ በክልሉ በቤተሰብ ደረጃ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ አማራጭ የኃይል አቅርቦት ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው።


 

በዚህም ከዋናው የኃይል ቋት ርቀው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የሶላር ፓኔል ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አባወራዎች መሰራጨታቸውን ገልጸዋል።

የታዳሽ ኃይል ልማትና ተደራሽነት የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ከዋናው የኃይል ቋት ርቀው የሚገኙ የገጠር የጤናና የትምህርት ተቋማት የኃይል አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በተጨማሪም በናፍጣ የሚሠሩ የውኃ ተቋማትን ወደ ፀሐይ ኃይል በመቀየር ኅብረተሰቡ ዘላቂ የመጠጥ ውኃ አገልግሎት እንዲያገኝ መሠራቱንም ጠቁመዋል።

በተያያዘም ከ700 ሺህ በላይ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችንና ከ1 ሺህ 500 በላይ የባዮ ጋዝ በመሥራት ለመብራት አገልግሎት እንዲሁም ተረፈ ምርቱ ለተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲውል መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም