በኦሮሚያ ክልል በመኸር እርሻ እስካሁን ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በመኸር እርሻ እስካሁን ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በመኸር እርሻው እስካሁን ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው ጀማነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በመኸር እርሻ 11 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በኩታገጠም በማልማት ከ380 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው።
በክልሉ እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ከ9 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በዘንድሮው የመኸር እርሻ ወቅት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በዋናነት የጥራጥሬ እና የሰብል ዘር ዓይነቶች እየተዘሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ታርሶ ለዘር ከተዘጋጀው መሬት ውስጥ እስካሁን 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታሩ በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ተሸፍኗል ብለዋል።
ለመኸር እርሻ ከተዘጋጀው መሬት ውስጥ እስካሁን ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው በትራክተር ታግዞ መታረሱን ጠቁመዋል።
በክልሉ ለመኸር እርሻ ሥራው ከ14 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ፣ እስካሁን ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ሕብረት ሥራ ማህበራትና በዩኒየኖች ጋር መድረሱን ገልጸዋል።
ለማህበራቱና ለዩኒየኖቹ ከደረሰው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሩ መከፋፈሉን አንስተዋል።
እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ይረዳ ዘንድ የተለያዩ ምርጥ ዘሮች ለአርሶ አደሮቹ መቅረባቸውን አክለዋል።
በክልሉ በአሁኑ ወቅት ያለው የዝናብ ሁኔታ መልካም በመሆኑ አርሶ አደሩ ያለውን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ በመጠቀም ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በክልሉ በመኸር እርሻው የታቀደውን ምርት ለማግኘት በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ ድጋፍና ክትትል እያደረጉላቸው ይገኛሉ ብለዋል።