ቀጥታ፡

በቀጣዩ  ዓመት በመዲናዋ የመንግሥት አገልግሎቶችን ሙሉ ለሙሉ በዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት ግብ  ተይዟል 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦በቀጣዩ ዓመት በመዲናዋ የመንግሥት አገልግሎቶችን ሙሉ ለሙሉ በዲጂታል አንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት ግብ መያዙን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል  አገልግሎት የዜጎችን እንግልት ከመቀነስ ባሻገር የመልካም አስተዳደር ችግሮች ትርጉም ባለው መልኩ እንዲቀነሱ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል።

 የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአቃቂ ቃሊቲ 10ኛውን፤  በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ደግሞ 11ኛውን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል። 


 

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ጃንጥራር አባይ፤የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድርን ጨምሮ የመዲናዋ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር የመንግሥት አገልግሎት ቢሮክራሲ፣ ውጣ ውረድ እና እንግልት የበዛበት እንደነበር አስታውሰዋል።


 

የመልካም አስተዳደር ችግር ዜጎች አገልግሎት በአግባቡ እንዳያገኙ ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን አመልክተው፤ የመሶብ አንድ  ማዕከል የዲጂታል አገልግሎት ለችግሮች ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን ገልጸዋል።

በቁርጠኝነት ከሰራን የማይለወጥ ነገር እንደሌለ በአንድ ማዕከል አገልግሎት ያመጣነው ውጤት ትልቅ ማሳያ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ ብልሹ አሰራር ከመሠረቱ እየተቀረፈ ነው ብለዋል።


 

የአገልግሎት ተደራሽነትን ይበልጥ ለማስፋት ዜጎች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው አገልግሎት የሚያገኙበት  ሂደት እንደሚጠናከርም ተናግረዋል። 

በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመንግሥት ከሚሰጡ አገልግሎቶች 50 የሚሆኑት ወደ አንድ ማዕከል እንዲገቡ መደረጉን ጠቅሰው፥ በቀጣዩ ዓመት ሙሉ ለሙሉ  ለማስገባት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አሁንም ቀሪ ስራዎች አሉ ያሉት ከንቲባ አዳነች፥ የዜጎችን እርካታ የሚያሳድጉ አገልግሎቶችን ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ለሕዝብ የገባነውን ቃል ወደ ተግባር እየቀየርን ብልጽግናችንን እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም