የብሩንዲው ፕሬዝዳንት ኤቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ብልፅግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
የብሩንዲው ፕሬዝዳንት ኤቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ብልፅግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፤ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ):-የብሩንዲው ፕሬዝዳንት ኤቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ብልፅግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የብሩንዲ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ኤቫሪሲቴ ንዳይሺሚዬ በህብረቱ እና በብሩንዲ ስም፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ለብልጽግና ፓርቲ ላስመዘገቡት ድል እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እወዳለሁ ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ይህ በምርጫ የተገኘው አዲስ የዲሞክራሲያዊ ውክልና ማረጋገጫ፣የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገሪቱን ወደ ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት እና የኢኮኖሚ ዕድገት ለመምራት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ላይ ያለውን ጥልቅ እምነትና መተማመን በተግባር ያሳየበት መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ታሪካዊት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ጠንካራ፣ የተባበረች እና የበለጸገች ሆና መቀጠሏ ለአህጉራዊው የጋራ አጀንዳችን ስኬት ምንጊዜም ቢሆን ወሳኝ መሠረት ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ኤቫሪስቴ በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ ብሩንዲ ከኢትዮጵያ ጋር ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከርና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን ለማጎልበት ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸው፥ ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካውያን መፍትሔ የሚለውን መርህ በጋራ ለማሳካት የጀመሩትን የቅርብ ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ይበልጥ የተባበረች፣የበለጸገች እና ሰላማዊ አፍሪካን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ፣ ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነትና አጋርነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።