መንግሥት በውጭ ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በትኩረት እየሠራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት በውጭ ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በትኩረት እየሠራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦ መንግስት የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መርህን በመከተል በውጭ ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ገለጹ።
በሳዑዲ አረቢያ የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ ምህረት የተደረገላቸው ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለስ ጀምረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪያድ የሚገኘውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሚሲዮን እና ጂዳ የሚገኘውን ቆንስላ ጽህፈት ቤት በማስተባበር ባደረገው የዲፕሎማሲ ጥረት በሳዑዲ አረቢያ ለእስር ተዳርገው የነበሩ ዜጎች የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ የምህረት አዋጅ እንዲሰጣቸው ማድረጉ ይታወቃል።
መንግሥት ምህረት የተደረገላቸው ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራን በይፋ መጀመሩን ተከትሎ የመጀመሪያዎቹ 320 ተመላሾች ዛሬ ወደ ሀገራቸው ገብተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ መንግስት ባደረገው ተከታታይ ጥረትና ክትትል ምህረት የተደረገላቸው ዜጎች እየተመለሱ ነው ብለዋል።
መንግስት የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መርህን በመከተል በውጭ ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለመታደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁን የተገኘው ውጤትም ላለፉት ሁለት እና ከዚያ በላይ ዓመታት ሲደረግ የቆየው ተከታታይ ዲፕሎማሲያዊ ክትትል ፍሬ መሆኑን ገልጸዋል።
ወደ ሀገር ከተመለሱት ዜጎች መካከል አብዛኛው በሀገራቸው ሰርተው መለወጥ የሚችሉ ወጣቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በሰው ሀገር ለእስርና ለእንግልት የተዳረጉት በተሳሳተ መረጃ እና በተለያዩ ምክንያቶች ህገ-ወጥ መንገድን በመምረጣቸው እንደሆነ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የሚተርፍ ሰፊ የስራ እድልና እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ትልቅ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።
በዚህም ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ ሰርተው ማደግና መብታቸው ተከብሮ መኖር የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መንግስት በሁሉም የልማትና የኢኮኖሚ ዘርፎች በትጋት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመላሾች በበኩላቸው ወደ ሀገራቸው ሲገቡ ከፍተኛ እፎይታና ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
መንግሥት ባደረገው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ምህረት ተደርጎላቸው ከእስርና የጭንቀት ህይወት ወጥተው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ በማድረጉም አመስግነዋል።