ቀጥታ፡

ጠቅላላ ምርጫው ቦርዱ የማስተናገድ፣ የመምራትና የመቆጣጠር ተቋማዊ ብቃቱን በተግባር ያሳየበት ነው

ጅማ ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የማስተናገድ፣ የመምራትና የመቆጣጠር ተቋማዊ ብቃቱን በተግባር ያሳየበት መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

የምርጫው ሂደት በሰለጠነ አግባብ የሃሳብ ፉክክር የታየበትና ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሰርአት ግንባታ ጥሩ መሰረት ያኖረ ነው ብለዋል።

በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ፣ የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለማረጋገጥ የሚደረግ ትልቅ ሀገራዊ ሁነት ነው።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ የምክር ቤት መቀመጫ በማግኘት አሸናፊ ሆኗል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በምርጫው ላሸነፈው ብልጽግና ፓርቲ መልካም ምኞታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ምርጫው የፖለቲካ ብስለት እንዲሁም የሕዝብን የሉዓላዊነት ስልጣን ባለቤትነት በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በጅማ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ፍቃዱ ቶለሳ (ዶ/ር)፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ መራጮች የተሳተፉበት፣ ነፃና ፍትሃዊ የፖለቲካ ፉክክር የተደረገበት ታሪካዊ ምርጫ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ለምርጫው ስኬታማነት ብዙ የሰራበትና በብቃት የመራበት ስለመሆኑ ታዛቢዎች ጭምር የመሰከሩለት ሆኗል ብለዋል።።

ለምርጫው የተሟላ ዝግጅት አድርጎ የማስተናገድ፣ የመምራት እንዲሁም የመቆጣጠር ከፍተኛ ተቋማዊ ብቃቱን በተግባር ያሳየበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የዲጂታል ምዝገባ እና የመረጃ አያያዝን ጨምሮ ሌሎችንም አሰራሮች በቴክኖሎጂ የታገዙ ማድረጉ፣ ዘመናዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ አስተዳደር ስርዓትን የመተግበር አቅሙን ተመልክተንበታል ብለዋል።

የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪ ሪያድ ዳውድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዘንድሮ ምርጫ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ መሰረት ያኖረ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ዜጎች በዲጂታል መንገድ ተመዝግበው የመራጭነት ካርድ እንዲወስዱ መደረጉ የምርጫ ተሳታፊዎችን ቁጥር ከፍ እንዲል አድርጓል ብለዋል።

እንደ አጠቃላይ ከዝግጅት ጀምሮ በቅድመ ምርጫው፣ በድምጽ አሰጣጡ እና በድህረ ምርጫው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የመራበት መንገድ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፎካከሩበት እና ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች የተመዘገቡበት የዴሞክራሲ ምህዳር ሰፍቶ የታየበት ስለመሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም