ቀጥታ፡

በመንግሥት የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሳዑዲ አረቢያ የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ ምህረት የተደረገላቸው ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለስ ጀመሩ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦መንግሥት በተከተለው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሳዑዲ አረቢያ የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ ምህረት የተደረገላቸው ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለስ ጀመሩ።

መንግስት የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መርህን በመከተል በውጭ ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪያድ የሚገኘውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሚሲዮን እና ጂዳ የሚገኘውን ቆንስላ ጽህፈት ቤት በማስተባበር ባደረገው የዲፕሎማሲ ጥረት በሳዑዲ አረቢያ ለእስር ተዳርገው የነበሩ 1 ሺህ 655 ዜጎች የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ የምህረት አዋጅ እንዲሰጣቸው ማድረጉ ይታወቃል።

መንግሥት ምህረት የተደረገላቸው ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራን ዛሬ በይፋ ጀምሯል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፤ መንግስት ባደረገው ተከታታይ ጥረትና ክትትል ምህረት ከተደረገላቸው 1 ሺህ 655 ዜጎች መካከል 320 የሚሆኑት የመጀመሪያዎቹ ተመላሾች ዛሬ ሀገራቸው ገብተዋል ብለዋል።

መንግስት የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መርህን በመከተል በውጭ ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለመታደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

አሁን የተገኘው ውጤትም ላለፉት ሁለት እና ከዚያ በላይ ዓመታት ሲደረግ የቆየው ተከታታይ ዲፕሎማሲያዊ ክትትል ፍሬ መሆኑን ገልጸዋል።

ወደ ሀገር ከተመለሱት ዜጎች መካከል አብዛኞቹ በሀገራቸው ሰርተው መለወጥ የሚችሉ ወጣቶች መሆናቸውን  ጠቅሰዋል።


 

በሰው ሀገር ለእስርና ለእንግልት የተዳረጉት በተሳሳተ መረጃ እና በተለያዩ ምክንያቶች ህገ-ወጥ መንገድን በመምረጣቸው እንደሆነ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የሚተርፍ ሰፊ የስራ እድልና እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ትልቅ ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል።

በዚህም  ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ ሰርተው ማደግና መብታቸው ተከብሮ መኖር የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መንግስት በሁሉም የልማትና የኢኮኖሚ ዘርፎች በትጋት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም