ቀጥታ፡

ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች ትምህርት ቤቶች የውስጥ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ዕድል ፈጥረዋል

ዲላ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ባለፉት ዓመታት የተከሏቸው ችግኞች የአካባቢን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የውስጥ ገቢያቸውን ለማሳደግ ዕድል መፍጠሩን በዲላ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ገለጹ።

በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች የተራቆቱ አካባቢዎችን ገጽታ በአረንጓዴ ከመሸፈን ባለፈ  ለውበትና ለገቢ ምንጭ እየሆኑ ነው።

በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከደን፣ ከጥላና ከውበት ዛፎች በተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለሚሆኑ ተክሎች ትኩረት መሰጠቱ ከመርሀግብሩ የሚገኘውን ጥቅም ዘርፈ ብዙ እያደረገው ነው።


 

መርሀግብሩ የተፋሰስ ልማት ከተከናወነባቸው ስፍራዎች በተጨማሪ በከተሞች ክፍት ይዞታዎችና በተቋማትም ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

በዲላ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በተከሏቸው ችግኞች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።   

ትምህርት ቤቶቹ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተከሏቸው ችግኞች የትምህርት ቤቱን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የውስጥ ገቢያቸውን እያሳደገው መምጣቱን ነው የተናገሩት። 


 

የዲላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደሳለኝ ታፈሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በትምህርት ቤቱ ያሉትን ባዶ ቦታዎች  በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ችግኞችን በመትከል የተሞክሮ ማዕከል ማድረግ ተችሏል።

በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በመርሀግብሩ የተተከሉ የቡና፣ የእንሰትና የፍራፍሬ ችግኞች የትምህርት ቤቱን ገጽታ እንደቀየሩና የውስጥ ገቢን እያሳደጉ መምጣታቸውን አንስተዋል።


 

በአሁኑ ወቅት ከቡናና ከፍራፍሬ ምርት ሽያጭ በዓመት ከ120 ሺህ ብር በላይ ገቢ ትምህርት ቤቱ እንደሚያገኝ ገልጸው፣ ልማቱ ተግባር ተኮር ትምህርት ለመስጠት ጭምር እየዋለ ነው ብለዋል።

አረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የትምህርት ቤታቸውን ባዶ ቦታ እንዲለማና ገቢ ማስገኛም ሆኗል ያሉት ደግሞ በዲላ ከተማ የዳዊት 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕስ መምህርት መሠረት ተሰማ ናቸው።


 

ለጥላ ዛፍ የሚሆኑ ዛፎች ከመተከላቸው በተጨማሪ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞች ለምርት መድረሳቸውን ጠቅሰው ይህም የውስጥ ገቢን በማሳደግ ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።

የዲላ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ ኡውዩ ሃይሉ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በከተማው ከ30 ሄክታር በላይ የትምህርት ቤቶች ይዞታ በአረንጓዴ አሻራ እንዲለማ ተድርጓል።


 

በተለይ ለምግብነት የሚሆኑ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ቡናና እንሰት የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ከመቀየር በተጨማሪ የገቢ ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመትም ይህንን ተሞክሮ በማስፋት ዘርፈ ብዙ ጠቄሜታ ያላቸውን ችግኞች በሌሎች ትምህርት ቤቶችም ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም