ቀጥታ፡

በክልሉ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት ይከናወናሉ

አሶሳ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት እንደሚከናወኑ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን አስታወቁ።

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ከ100 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካማ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ግንባታና እድሳት እንደሚከናወንም ተገልጿል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በአሶሳ ከተማ በአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ እና በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ስራ ተጀምሯል።


 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በየዓመቱ የሚካሄደው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውንና አቅመ ደካማ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። 

ክልሉ ሰፊ የገጠር አካባቢዎችንና በተለያዩ ምክንያቶች የኢኮኖሚ አቅማቸው የደከሙ ዜጎችን የሚያሻሽል መኖሪያ ቤት ተደራሽ ለማድረግ በየዓመቱ ዕቅዶችን ቀርጾ ይንቀሳቀሳል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ እንዳሉት፤ በተያዘው ክረምት በሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረጉ እና የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቁ ተግባራት ይከናወናሉ።


 

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት ከ 2ሺህ 300 በላይ ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸውን ገልፀው፥ በዚህ ዓመትም ከ100 በላይ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።

የሚገነቡ ቤቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለተጠቃሚዎች እንዲተላለፉ ተገቢው ክትትል እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

እንዲሁም የተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ ማዕድ ማጋራት እና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።

በማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፡ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ፣ የክልሉ ምክርቤት አፈጉባኤ አስካለች አልቦሮ፣ በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር እንዲሁም የአሶሳ ከተማ አመራሮች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም