ቀጥታ፡

መንግሥት የኮንስትራክሽን ዘርፉን ጥራት፣ ደኅንነትና ዘላቂነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦ መንግሥት የኮንስትራክሽን ዘርፉን ጥራት፣ ደኅንነትና ዘላቂነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን የጸደቁ አዲስ የሕንፃ ኮዶችና ስታንዳርዶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል ሀገራዊ መድረክ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሀመድ አብዶ፣ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲና የምርምር ተቋማት አመራሮች፣ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች እንዲሁም የሙያ ማህበራት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ መንግሥት የኮንስትራክሽን ዘርፍን ጥራት፣ ደኅንነትና ዘላቂነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ እንዲሁም አጠቃላይ ተቋማዊ ሪፎርምና ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።

የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የሀገር ልማት ዋና ሞተሮች ቢሆኑም፣ መሠረተ ልማቶችን በጥራትና በደኅንነት በመገንባት የኢኮኖሚ አቅም እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የግንባታ ደኅንነት በሳይንስ፣ በምህንድስና ስታንዳርዶች ሥርዓት ላይ ተመስርቶ በመሥራት የሚመዘገብ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

አዲሶቹ ኮዶችና ስታንዳርዶች ዓለም አቀፍ የምህንድስና ልምዶችንና የምርምር ውጤቶችን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን አንስተዋል።

እንዲሁም የአየር ንብረት ሁኔታ፣ የጂኦሎጂ ባህሪያትና የልማት ፍላጎቶችን ያገናዘቡ ብሔራዊ መለኪያዎች የተካተቱባቸው በመሆኑ ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በተጣጣመ መልኩ እንደተዘጋጁ ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በአሁኑ ወቅት በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሕግና የቁጥጥር ሥርዓትን ማዘመን፣ አሠራርን ዲጂታላይዝ ማድረግ፣ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማጠናከር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማስፈን ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኮድና ስታንዳርዶቹ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ወጥና ደረጃውን የጠበቀ አሠራር ይፈጥራሉ ብለዋል።

ለተግባራዊነታቸው የሁሉም አካላት ርብርብና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም