ከብልጽግና ፓርቲ ጋር የጀመርነውን የልማትና የሀገረ መንግስት ግንባታ ተግባራትን አጠናክረን እንቀጥላለን - ኢዜአ አማርኛ
ከብልጽግና ፓርቲ ጋር የጀመርነውን የልማትና የሀገረ መንግስት ግንባታ ተግባራትን አጠናክረን እንቀጥላለን
ሐረር፤ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦በምርጫው አሸንፎ መንግሥት ከሚመሰርተው ብልጽግና ፓርቲ ጋር የተጀመሩ የልማትና የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሐረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ይፋ አደረገ።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሀሰነት ሙሜ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ውጤት መሠረት 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የብልፅግና ፓርቲ በአብላጫ የምክር ቤቶች መቀመጫ አሸንፏል።
ሰብሳቢዋ ህዝብ ይሆነኛል ብሎ ለመረጠውና አሸናፊ ለሆነው የብልፅግና ፓርቲ፣ እንዲሁም በምርጫው ተሳትፈው በምክር ቤቱ ወንበር ላገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤቱ ስም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሕዝብን የሉዓላዊነት ሥልጣን ያረጋገጠውን የምርጫ ሂደት፣የተሰጠውን የሕዝብ ድምፅና የተመዘገበውን የሕዝብ ድል የሚያከብሩ መሆናቸውንም ሰብሳቢዋ አክለው ገልጸዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ቀደም ሲልም በሰላምና የልማት ስራዎች፣በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣በሪፎርምና በሌሎች ስራዎች ከመንግስት ጋር ተባብሮ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በቀጣይም የጋራ ምክር ቤቱ በምርጫ አብላጫ ድምጽ ካገኘውና መንግስት መስርቶ ሀገር ከሚመራው ብልጽግና ፓርቲ ጋር የተጀመረውን ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በተሻለ መልኩ እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በሀገሪቱ በርካታ የልማትና ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎችን ማከናወኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም ለሀገር የሚጠቅም እውቀትና ክህሎት ያላቸውንና በምርጫው ሂደት እድሉን ያላገኙ አባላትን የማካተት ስራ እንዲከናወን ጠይቀዋል።
እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱን በቁሳቁስ የማጠናከርና ለአባላቱ አቅም ማጎልበት ላይ የድጋፍ ስራ እንዲከናወን መልዕክት አስተላልፈዋል።