በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ አስተዋፅኦ አበርክቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ አስተዋፅኦ አበርክቷል
ዱራሜ ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ክልላዊ የክረምት ወራት አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በዱራሜ ከተማ አስጀምረዋል።
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትግበራ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ተግባሩም የአፈር ለምነትን በማስጠበቅና በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰቱ ችግሮችን በመከላከል የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት እንዲመዘገብ ማድረጉን አስረድተዋል።
የማህበረሰቡ ችግኝን የመትከል ብቻ ሳይሆን የመንከባከብ ባህል እያደገ ስለመምጣቱም ጠቁመዋል።
በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠልም የዘንድሮው የክረምት ወራት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በይፋ መጀመሩን አብስረዋል።
በክልሉ በዘንድሮው የክረምት ወራት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ530 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉም ጠቁመዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይም የክልል ፣ የዞንና የልዩ ወረዳ አመራሮች ተገኝተዋል።