የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ስኬታማ የሚያደርጉ ጉልህ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ስኬታማ የሚያደርጉ ጉልህ ተግባራት ተከናውነዋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ስኬታማ የሚያደርጉና ተቋማዊ ሪፎርምን የሚያረጋግጡ በርካታ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ ገለጹ፡፡
በተለይም ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬታማነት መጠናቀቁ የዚሁ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት የዴሞክራሲ መሠረት የሆኑ ነጻና ገለልተኛ ተቋማትን ለመገንባት ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
ለዚህም ስኬት ተቋማቱ ሙሉ ነጻነት ኖሯቸው እንዲንቀሳቀሱ ያስቻሉ ሥር ነቀል የሕግ ማሻሻያዎች፣ የአደረጃጀት ለውጦች እና የአቅም ግንባታ ሥራዎች በስፋት ተተግብረዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ እንደገለጹት፤ ምክር ቤቱ ባለፉት አምስት ዓመታት የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ለማጠናከር ስትራቴጂካዊ ሚና ተጫውቷል።
ከለውጡ በፊት የነበሩ፣ የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጋፉ ሕጎችን ለመቀየርና የማሻሻል ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት መሠረት መጣሉን ተናግረዋል፡፡
የዴሞክራሲ ተቋማት ሥር ነቀል የሪፎርም ሥራዎችን እንዲያከናውኑ መደረጉን የጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ ለሥራቸው ምቹ ምኅዳር የሚፈጥሩ የሕግ ማሻሻያዎች፣ የአደረጃጀት ለውጦች እና ዲጂታላይዜሽንን የማስፋፋት ሥራዎች በስፋት መተግበራቸውን አስረድተዋል።
ተቋማቱ ሙሉ ነጻነትና ገለልተኝነት ኖሯቸው እንዲንቀሳቀሱም ብቃት ባለው የሰው ኃይልና አስፈላጊው ግብዓት እንዲደራጁ ድጋፍ መደረጉን አክለዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሂደቱ በሀገር ግንባታ ላይ የዜጎችን ተሳትፎ የሚያሳድግና አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑ እስከ አሁን ያከናወናቸው ተግባራት እጅግ አካታች በሆነ መንገድ መካሄዱን አንስተው፤ ወደፊት በሚካሄደው ዋናው የምክክር ጉባኤ ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎች የሀገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመወሰን ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ በበኩላቸው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገሪቱ ታሪክ ታይተው የማይታወቁ ተስፋ ሰጪ የዴሞክራሲ ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የዴሞክራሲ ምኅዳሩን የሚያሰፉ በርካታ የሕግ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ጠቅሰው፣ በተለይም የምርጫ ሕጉ መሻሻሉን ለአብነት አንስተዋል።
ምክር ቤቱ በውክልና ሥራው የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በየደረጃው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ባከናወናቸው ሥራዎች አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በስኬት የተጠናቀቀው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መጎልበቱን በተግባር ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡