የሀዋሳ ቀጣይ የዕድገትና የውበት ምዕራፍ - ኢዜአ አማርኛ
የሀዋሳ ቀጣይ የዕድገትና የውበት ምዕራፍ
ሀዋሳ፤ ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦የሀዋሳ ቀጣይ የዕድገትና የውበት ምዕራፍ
በእንዳለ ደበላ (ሀዋሳ ኢዜአ)
ታቦር ተራራን በአንድ ጎኗ አላሙራ ተራራን ደግሞ በሌላው ጎኗ ታቅፋ የከተመችው ሀዋሳ ከተማ የፍቅር ሐይቅን ጨምሮ የተለያዩ የመስህብ ስፍራዎችንም በጉያዋ አቅፋ ይዛለች።
ለባህላዊ ሕክምና አገልግሎት ጭምር የሚውሉት የወንዶገነት እና የይርጋለም የተፈጥሮ ፍል ውሀዎች ከሀዋሳ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘታቸው ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን በማድረግ በኩል የራሳቸው አስተዋጽኦ አላቸው።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መዲናዋ ሀዋሳ ካሏት ተፈጥሯዊ የመስህብ ስፍራዎች በተጨማሪ የተለያዩ ባህላዊና ሀይማኖታዊ በዓላት በድምቀት የሚከበሩባት መሆኑም በጎብኚዎች ተመራጭ አድርጓታል።
ሀዋሳ ባላት የተፈጥሮ ሀብት ላይ ተጨማሪ ውበትን ያላበሳት የኮሪደር ልማትም ከተማዋን ለኑሮ፣ ለሥራና ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹና ተመራጭ እያደረጋት ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደከተማዋ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር እንዲበራከትና የቆይታ ጊዜያቸውንም እንዲያራዝሙ በማድረግ በኩል የኮሪደር ልማቱ አዎንታዊ ሚና መጫወት ጀምሯል።
በከተማዋ ከሪፈራል ሰርክል እስከ መንቦ፣ ከሳውዝ ስፕሪንግ እስከ ፍቅር ሐይቅ፣ ከፍቅር ሐይቅ እስከ ሳውዝ ስታር ሆቴል የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በተፈጥሮ የታደለችውን ሀዋሳን የበለጠ አድምቋታል። ውበቷን አጉልቶ ከማውጣት በተጨማሪ የከተማዋ ገቢ በማሳደግ በኩልም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው።
የሲዳማ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ምክትል ሀላፊና የደንበኞች አገልግሎት የታክሰ አሰባሰብ ዘርፍ ሀላፊ ወይዘሮ ሙላት ዮሴፍ በእዚህ ሀሳብ ይስማማሉ። እሳቸው እንዳሉት ባለፉት 11 ወራት በከተማዋ 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል።
አምና በተመሳሳይ ወቅት 5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደተሰበሰበ አስታውሰው የዘንድሮው 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው ብለዋል። ለገቢው መጨመር በምክንያትነት ከጠቀሷቸው አንዱ የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የንግድ እንቅስቃሴውና የጎብኚው ቁጥር እያደገ መምጣት ነው።
ይህን የከተማዋን የገቢ አቅም የበለጠ ለማሳደግ ያስችላል የተባለለት ተጨማሪ የኮሪደር ልማትም በአሁኑ ወቅት ሥራው ተጀምሯል። ከሳውዝ ስታር ሆቴል በቀድሞው መናኸሪያ እስከ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ አንዱ ሲሆን በፍጥነት ለማጠናቀቅም ታቅዶ እየተሰራ ነው።
ሀዋሳ የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከልነቷልን ይበልጥ ለማሳደግ አሁንም በትጋት እየሰራች ነው፤ አሁንም ልማት ላይ ነች። ከከተማዋ መግቢያ የሐይቅ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ታቦር ተራራ ድረስ 12 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የሐይቅ ዳርቻ ልማት ተጀምሯል። ይህም የከተማዋን እድገት ከማስቀጠል ባለፈ ይበልጥ የሚያደምቃት ነው። ተመራጭነቷነም ከፍ ያደርገዋል።
በስድስት ወራት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ታቅዶ ወደሥራ የተገባው የሐይቅ ዳርቻ የኮሪደር ልማት በመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራ የፍቅር ሐይቅ መግቢያ፣ አሞራ ገደል እና አሣ ገበያ አካባቢዎችን አካቶ የሚገነባ ነው።
የሐይቅ ዳርቻ ልማቱ 60 ሜትር ወደ ሐይቁ ተገብቶ የሚከናወን ሲሆን ሰው ሰራሽ የውሀ ፏፏቴ፣ በሐይቁ ዳርቻ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ፣ የተለያዩ ሱቆች፣ ሬስቶራንት፣ የመመልከቻ ማማዎች እንዲሁም ሌሎች መዝናኛዎችን አካቶ የሚሰራ ነው። ልማቱ ተጠናቆ ወደአገልግሎት ሲገባ በከተማዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ አዎንታዊ አበርክቶ ይኖረዋል።
የከተማዋ የቱሪዝም መረጃ እንደሚያሳየው ካለፉት ዓመታት ወዲህ በሀዋሳ ከተማ የቱሪስት ፍሰት እየጨመረ መጥቷል። በተለይ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ረገድ እና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በኩል እየታየ ያለው ለውጥ ከተማዋን በቱሪስቶች ይበልጥ ተመራጭ አድርጓታል።
ሀዋሳ ከተማ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ጨምሮ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማስተናገድ ተመራጭ መሆኗ በስፖርት ቱሪዝም ዘርፍ ይበልጥ እንድትታወቅ እያደረገ ነው። ክለባቸውን ለመደገፍ ወደከተማዋ የሚመጡ ደጋፊዎች ዘርፉ እንዲነቃቃ የራሳቸውን አሻራም እያሳረፉ ይገኛሉ።
በሀዋሳ ከተማ የሚከበሩ ሀይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትም ከተማዋ በርካታ እንግዶችን እንድታስተናግድ ከማድረጋቸው ባለፈ ለከተማዋ ገቢ መጨመር የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የሲዳማ ዘመን መለወጫ በዓል (ፊቼ ጨምበላላ) ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስበው ይሄ በዓል ሌላው የሀዋሳ ከተማ ድምቀት ነው።
በየዓመቱ በፍቼ ጨምባላላ በዓል ላይ ለመታደም ከሀገር ውስጥና ከመላው ዓለም በርካቶች ወደሀዋሳ ከተማ ስለሚመጡ ዋነኛው የቱሪስት መስህብ ነው ማለት ይቻላል።
እነዚህ ባህላዊ፣ ሀይማኖታዊና ተፈጥሯዊ እሴቶችን በአግባቡ በማልማትና በማጎልበት ሀዋሳን ይበልጥ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በቅርቡ የግንባታ ሥራው የተጀመረው የሀዋሳ ፍቅር ሐይቅ ዳርቻ ልማት ለእዚህ አንድ ማሳያ ነው። ልማቱ ከተማዋን የሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ብሎም የዓለም ኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ ትልቅ ራዕይ ይዞ የተጀመረ ነው።
ይህን የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ የኮሪደር ልማት በይፋ ያስጀመሩት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ናቸው። የፍቅርና የሕብር ተምሳሌት የሆነችውን ሀዋሳ ውበቷን ይበልጥ ለማውጣትና ተመራጭ ለማድረግ የክልሉ መንግስት አበክሮ ይሰራል ነው ያሉት።
እንደእሳቸው ገለጻ የኮሪደር ልማት ሥራው በፍጥነት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይም ከሀዋሳ ሐይቅ እስከ ሞኖፖል ድረስ ያለውን አካባቢ በአምስተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ለማልማት ታቅዷል።
ሀዋሳን የኮንፈረንስ፣ የስፖርትና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ትልቅ ዕድል ይዞ ለሚመጣው የሀዋሳ ሀይቅ ዳርቻ ልማት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
የሀዋሳ ከተማን በሀገር ውስጥና በአፍሪካ ተመራጭ የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ እንደሚሰራ የገለጹት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጥራቱ በየነ ናቸው።
ከተማዋን ይበለጥ ተመራጭ ለማድረግ ለሚከናወነው የመጀመሪያ ዙር የሐይቅ ዳርቻ ልማት 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን የሚሆው ከማህበረሰቡ የሚሰበሰብ መሆኑን ነው ከንቲባው የገለጹት።
ህዝቡም የከተማዋን ልማት ለመደገፍ የአቅሙን እያገዘ ነው። ለልማቱ በአይነት፣ በገንዘብና በዕውቀት እያደረገ ያለው ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።
የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ከ1 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ያነሱት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሀዋሳ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ቸርነት ፍላቴ ናቸው።
በሀዋሳ በተለያዩ ምዕራፎች የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እስካሁን ከ2ሺህ ለሚበልጡ ሰዎቸ የሥራ ዕድል በመፍጠር ለበርካቶች ተጨማሪ ጥቅምን አስገኝቷል።
የልማት ሥራዎች ለከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ሀዋሳን ውብ፣ ምቹና ለኑሮ ተመራጭ ከተማ እያደረጓት በመሆኑ በቀጣይም ህብረተሰቡን በማሳተፍ ልማቱ እንደሚጠናከር ነው የገለጹት።
ከታቦርና አላሙራ ተራሮች እግር ሥር የከተመችው ሀዋሳ ዛሬም በሥራ ላይ ናት፣ የሚሰሩ ልጇቿ ዛሬም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ከተማዋን ይብልጥ ከፍ ለማድረግ እየታተሩ ነው። የከተማዋን የቀጣይ የዕድገትና የውበት ምዕራፏን እውን ለማድረግ ልጆቿ በአቅማቸው አሻራቸውን ለማሳረፍ ወደተግባራዊ ሥራ ገብተዋል። በማማዋ ላይ ከፍ ብላ ጎልታ እንድትታይ የሚያደርጉት ርብርብ በዚህ ከቀጠለ ራዕዩዋን በማሳካት ሀዋሳን ከሀገር ውስጥ ባለፈ የአፍሪካ ኮንፈረንስ ማዕከል የማድረግ ግብ መሳካቱ አይቀሬ ነው።