ቀጥታ፡

የስማርት ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል መከላከልና ምርመራ አገልግሎትን በማቀላጠፍ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦የስማርት ፖሊስ ጣቢያ የፖሊስ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወነ ባለው ሀገራዊ የሪፎርም ሂደት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ገለጸ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በየካቲት ወር 2018 ዓ.ም በአፍሪካ የመጀመሪያውን ሰው አልባ ስማርት የፖሊስ አገልግሎት Smart Police Station (SPS) መርቀው ሥራ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት፤ ይህ አገልግሎት ዜጎች የፖሊስ አገልግሎትን በተሻለ ፍጥነት እና በቴክኖሎጂ ታግዘው እንዲያገኙ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም አገልግሎቱ ለፖሊስ ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለው እና የወንጀል መከላከል ሥራውን የሚያቀላጥፍ መሆኑን መጥቀሳቸው ይታወቃል፡፡

አገልግሎቱ የፖሊስ አገልግሎትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስደገፍና የሕዝብን ተሳትፎ በማሳደግ የወንጀል መከላከልና የሕግ ማስከበር ሥራን በማገዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተቋማት ኦፕሬሽን ክፍል ዋና ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አንድነት ሲሳይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሰው አልባ የስማርት የፖሊስ አገልግሎቱ ዜጎች በአካል ተገኝተው መዝገብ የሚከፍቱበትንና አገልግሎት የሚጠይቁበትን የቀደመ አሠራር ወደ ዘመናዊ ዲጂታል ሥርዓት የቀየረ ነው።


 

ይህ አዲሱ አሠራር ያለምንም የፖሊስ ኃይል በቀጥታ ሙሉ በሙሉ በዲጂታል መንገድ አገልግሎቱን መስጠት የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።

አገልግሎቱ ወደ ጣቢያው የሚመጡ ባለጉዳዮች በቴክኖሎጂው ታግዘው ጉዳያቸውን በራሳቸው ማከናወን እንዲችሉ እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም በርቀት የሚገኝ ባለሙያን በቪዲዮ ስክሪን በቀጥታ ማግኘት እንዲችሉ በማድረግ በቀላሉ አገልግሎቱን እያገኙ መሆኑን ጨምረው ጠቁመዋል።

በጣቢያው ዙሪያ የተገጠሙ ስማርት የደህንነት ካሜራዎችም በተለይ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ችግር እንዳይገጥማቸው ድጋፍ ለማድረግ እያገዘ መሆኑን ጨምረው አንስተዋል።

በአጠቃላይ አዲሱ አሠራር ዜጎች ጉዳያቸውን ደህንነትና ሚስጥራዊነት በተጠበቀ ሁኔታ ማቅረብና አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን ትልቅ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የቴክኖሎጂ ማስፋፊያና የዜጎች ተሳትፎ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር ዓለሙ ተሰማ በበኩላቸው፤ በሀገራዊ ፖሊስ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ከብቁ የሰው ኃይል ጋር አቀናጅቶ የሚጠቀም ተቋም መፈጠሩን ገልጸዋል።


 

ይህም ሰው አልባ የስማርት ፖሊስ አገልግሎት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ አገልግሎቱን የማቀላጠፍ አካል መሆኑን አንስተዋል።

አገልግሎቱ ወደ ተግባር ከገባ ጀምሮ ሕዝቡ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ጥቆማ እንዲሰጥ እያስቻለ ሲሆን የወንጀል መከላከል ሥራን ውጤታማነት እያጎለበተ ይገኛል ብለዋል።

የስማርት ፖሊስ ጣቢያ (Smart Police Station (SPS) ) መጀመር በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የሕግ አስከባሪ አካላት ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተጀመረውን የሪፎርም ሥራ ውጤታማነት የሚያሳድግ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም