ስልጡን የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ የሲቪክ ማህበራት ሚናቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ስልጡን የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ የሲቪክ ማህበራት ሚናቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦ለሃገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ አማራጭ ሃሳቦች እንዲተገበሩና ስልጡን የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ የሲቪክ ማህበራት ተቋማዊና ሙያዊ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሁሴን ገለጹ።
የመንግስትና የሲቪል ማህበራት የጋራ የትብብርና ቅንጅት መድረክ ሀገራዊ ዲሞክራሲን በትብብርና በጋራ ለመገንባት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መድረክ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሁሴን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የበኩላቸውን ሚና ተወጥተዋል።
ማህበራቱ የመራጮች ትምህርት በመስጠት፣ስልጠናዎችን በማመቻቸትና ምርጫውን በንቃት በመታዘብ ሂደት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ምርጫ መንግስት የሚመሰረትበት ሂደት መሆኑን አውስተው፤ለህብረተሰቡ ምርጫ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ፣ እኩልነትና ተጠያቂነት የሚረጋገጥበት መሆኑን ለማስገንዘብ ተሰርቷል ብለዋል።
ሕዝቡ በምርጫ ወቅት በከፍተኛ ተነሳሽነትና በንቃት መሳተፉ ለዘላቂ ሰላም፣ደህንነትና ከድህነት ለመውጣት ያለውን ፅኑ ፍላጎት ያሳየበት መሆኑን አቶ አህመድ አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ ለሚታዩ አለመግባባቶችና ቅሬታዎች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት፣በሀገራዊ ምክክሩ ስራዎች ላይ ሁሉም አካላት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በምርጫ ማግስት ያለው ጊዜ እውነተኛ የዲሞክራሲ ባህል በተግባር የሚፈተንበት ወቅት መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሲቪል ማህበራት፣ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ምክር ቤቱ በቀጣይም በሂደቱ የታዩ ክፍተቶችን በጥናት በመለየት፣ የተሻሉ አማራጭ ሀሳቦችን ለፌዴራልና ለክልል ምክር ቤቶች ለማቅረብ ሙሉ ዝግጁነት እንዳለው አረጋግጠዋል።
የመንግስትና የሲቪል ማህበራት የጋራ የትብብርና ቅንጅት መድረክ መኖሩን ጠቅሰው፥ በቀጣይ ዲሞክራሲን በትብብር ለመገንባት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።
ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ አማራጭ ሃሳቦች እንዲተገበሩና ስልጡን የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ የሲቪክ ማህበራት ተቋማዊና ሙያዊ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
በእውነተኛ የዲሞክራሲ ባህል በምርጫ አንዱ አካል ማሸነፉ የሌሎችን አማራጭ ሃሳብ ውድቅ ያደርጋል ማለት አይደለም ያሉት አቶ አህመድ፤ ለሀገር የሚጠቅሙ የየትኛውም አካል ሀሳቦች በአሸናፊው መንግስት ሊወሰዱ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በትብብር መንፈስ አማራጭ ሀሳቦችን በማቅረብ በህግ ማውጣት ሂደት ላይ በጎ ተፅዕኖ ማሳደር እንዳለባቸው ገልፀዋል።