ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን አጠናክሮ ለማስቀጠል በቂ ዝግጅት ተደርጓል 

ሐረር ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ካስገኛቸው ጠቀሜታዎች መካከል የሥራ ዕድል አንዱ ሲሆን በዚህ ረገድ የተሰማሩ ዜጎችም ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የደን ሽፋንን ለማሳደግ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ታስቦ በሀገር አቀፍ ደረጃ በስፋት እየተተገበረ የሚገኝ ብሔራዊ ንቅናቄ ነው። 

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በየክረምቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ረገድ ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበበት ይገኛል።


 

የሐረሪ ክልል ምንም እንኳን በቆዳ ስፋቱ አነስተኛ እና የከተማ ግብርና የሚበዛበት ክልል ቢሆንም፣ ባለፉት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄን ከተማን ከማስዋብ፣ የውሃ አማራጮችን ከመጠበቅና የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ከማልማት አኳያ በልዩ ትኩረት ሲተገበር  ቆይቷል።

በተለይም በክልሉ የሚስተዋለውን የውሃ እጥረት ለመቅረፍ እና የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን ለማገዝ በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች የመጽደቅ ምጣኔን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል። 

በክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ አራርሶ አደም ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል።

ለተከላ ከተዘጋጁ ችግኞች ውሰጥ 70 በመቶ የሚሆኑት አትክልትና ፍራፍሬ መሆናቸውንና ቀሪዎቹ ደግሞ ለደንና ለእንሰሳት መኖነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

አብላጫው ችግኞች በአርሶ አደር ማሳ ውስጥ የሚተከሉ መሆኑን ጠቁመው፤  ቀሪዎቹ  የደንና ለእንስሳት መኖነት የሚያገለግሉ ችግኞች ደግሞ በተፋሰሶች፣ እርከኖችና ሌሎች ስፍራዎች ላይ እንደሚተከሉ ገልጸዋል።

በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በነገው እለት ሰኔ 18  ቀን 2018 ዓ.ም  በይፋ እንደሚጀመርም  ጠቁመዋል።


 

ቀደም ሲል ችግኝ መትከል እንጂ መንከባከብ ላይ ትኩረት አይሰጥም ነበር ያሉት ደግሞ በክልሉ ቂቅሌ ችግኝ ጣቢያ ፎርማን አቶ ምንዳ ጥላሁን ናቸው።

አርሶ አደሩ ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚያገኘው ጠቀሜታ በተጨባጭ ውጤት ስላስገኘለትና የችግን ጥያቄዎቹም እያደጉ ስለሚገኝ እኛም የችግኝ ዝግጅት ስራን ከዓመት ዓመት እያሳደግን እንገኛለን ብለዋል።


 

በችግኝ ዝግጅት ላይ በመሰማራት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ ኢፍቱ አልይ ፤ በችግኝ ዝግጅት ስራ በመሰማራቴ ሀገሬን አረንጓዴ እያለበስኩ ነው፤ በግሌም ተጠቃሚ ሆኛለሁ ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ማዘጋጀት ተግባር ተሰማርቼ  ተጠቃሚ ሆኛለሁ፤  ልጆቼን አስተምራለሁ ኑሮዬንም እያሻሻልኩበት ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ መይሙና ያሲን ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም